
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰጠናቸውን ከ1 ሺህ በላይ ሰልጣኞች ዛሬ አስመርቋል።
የባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ፈለቀ ውቤ እንዳሉት ኮሌጁ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት፣ የአሽከርካሪዎች እና የቴክኒሻን ስልጠና እንዲሁም በዲግሪ መርሐ ግብር ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።
በዛሬው እለትም ከ1 ሺህ በላይ በቴክኒክና ሙያ ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች አስመርቋል።ከዚህ ውስጥ 160 በዲግሪ መርሐ ግብር የሰለጠኑ ናቸው። በ2015 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀንና በማታ፣ ለ17 ሺህ ሰልጣኞች ደግሞ አጫጭር ሥልጠናዎችን መሠጠቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በኮሌጁ የሰለጠኑ ሰልጣኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አቶ ፈለቀ አንስተዋል። ባለፈው ዓመት በኮሌጁ ከሰለጠኑ 1ሺህ 400 ተመራቂዎች መካከል 75 በመቶ የሚኾኑት የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ለአብነት አንስተዋል። የአሁን ሰልጣኞችም ሥራ ፈጠራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኮሌጁ አሁን ላይ በስድስት ዋና ዋና የስልጠና ዘርፎች፣ በ14 የትምህርት ክፍሎች እና ከ65 በላይ የሙያ አይነቶች ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት በማታና በመደበኛ መርሐ ግብር በማሰልጠን ላይ ይገኛል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ድረስ ሳህሉ ኮሌጁ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለኢንዱስትሪው እድገት መካከለኛ ባለሙያዎችን በማፍራት ሰፊ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።
ተወዳዳሪ ተማሪዎችን በማፍራትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ኮሌጆች አንዱ መኾኑን አንስተዋል። ከዚህ በፊት በኮሌጁ ተምረው በተለያዩ የሥራ መሥክ ላይ የተሠማሩ ሰልጣኞች ባቀረቡት ፈጠራ በፌደራል ደረጃ በተካሄደው ውድድር ክልሉ በቀዳሚነት እንዲቀመጥ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም ሰልጣኞች ፈጠራ ላይ በማተኮር ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰልጣኞችም በትምህርት ቆይታቸው የሙያ ክህሎትን ማዳበር መቻላቸውን ገልጸዋል። በተማሩበት ዘርፍም የግል ሥራ በመፍጠር ለመሥራት መዘጋጀታቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!