በዋሽንግተን ዲሲ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀት ነገ ይቋቋማል፡፡

192

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 18/2012ዓ.ም (አብመድ) ከነገ ዕሁድ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የአልማ አደረጃጀቶች እንደሚቋቋሙ የጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሰሜን አሜሪካ ከሕዝብ ጋር ባካሄዷቸው ምክክሮች ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ አልማን በዘላቂነት መደገፍና ለዚህም የሚያመች አሰራር እንዲኖር ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ምክክር በተደረገባቸው ግዛቶች ሁሉ ጊዜያዊ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከነገ ታኅሳስ 19/2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለሁለት ዓመታት የሚሰሩ መሪዎች እንደሚመረጡ የአደረጃጀቱ ጊዜያዊ ሰብሳቢ ብርጋዲዬር ጀነራል መላኩ ሽፈራው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ነገ ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ ሰባት አባላት ያሉት የአልማ አደረጃጀት መሪዎች በዋሽንግተን ዲሲ ይመረጣሉ፤ በሌሎች ግዛቶችም በመርሀ ግብሮቹ መሠረት ምርጫው ይከናወናል፡፡ አንደ ብርጋዲዬር ጀነራል መላኩ ገለጻ በዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደውን ምርጫ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ጊዜያዊ አደራጆች እና የአማራ አደረጃጀቶች በቀጥታ እንዲከታተሉት፣ ልምድ እንዲያገኙ እና እንዲካፍሉም ይደረጋል፡፡

በዕለቱ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ደግሞ በአማራ ክልል የዳስ ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር የሚያግዝ ገቢ ለማሰባሰብ የሙዚቃ ዝግጅት እና የእራት ግብዣ መርሀ ግብር ይካሄዳል፡፡ በዝግጅቱም ታዋቂ አርቲስቶች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፤ ምሁራን፣ ባለሃብቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችም በክብር እንግድነት እንደሚገኙ መርሀ ግብሩ ያሳያል፡፡

ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ-ከዋሽንግተን ዲሲ

Previous articleኢዜማ ከ400 በላይ ወረዳዎችን ያካተተ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
Next articleበዓለም በየቀኑ ከ800 በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያልፋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 59 በመቶ የሚሆኑት ለሞት የሚዳረጉት ግጭት በሚያስከትለው ዳፋ ነው፡፡