በላይነህ ክንዴ ፋንውዴሽን በፍኖተ ሰላም ከተማ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለኾኑ ወገኖች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ።

60

ፍኖተ ሰላም: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በላይነህ ክንዴ ፋንውዴሽን በፍኖተ ሰላም ከተማ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለኾኑ ወገኖች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረክቧል።

በላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን 10 የአቅመ ደካማ የመኖሪያ ቤቶችን ነው ገንብቶ ያስረከበው። ቤቶቹ የጋራ መፀዳጃና የሻወር አገልግሎት ያላቸው ናቸው።

ወይዘሮ መሠረት አድማሱ በደሳሳ ጎጆ ልጆችን ይዘው በችግር ይኖሩ እንደነበር ነው ያስታወሱት፣ አሁን ላይ ደሳሳ ጎጇቸው ቀርታ በመልካም ቤት መኖር እየጀመሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ ከችግር አውጥተው በሞቀ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ እንዳስቻሏቸው ነው የገለጹት። ዝናብ የሚያፈስስ፣ ፀሐይ የሚያጠቃው ቤታቸው አሁን ላይ የለም ፣ አሁን ላይ በጥሩ ቤት ጥሩ ኑሮ መኖር ጀምረዋል። ገንብተው ያስረከቧቸው ባለሀብት በላይነህ ክንዴንም አመሥግነዋል። በመከራ ጊዜ እንደደረሱላቸው ነው የተናገሩት። ሌሎች ባለሀብቶችም በችግር ውስጥ ሆነው በክረምት ዝናቡ፣ በበጋ ፀሐዩ እያሰቃያቸው የሚኖሩ ወገኖችን እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ዘይት ምህረት ይሄን ቤትስ አስበነውም አናውቅ ነበር ፤ ከዚያ ቤት ወጥተን እዚህ ገብተናል፣ ልብ ይመርቅ ልባችን መርቆታል፣ ጨምሮ ጨምሮ ይስጠው፣ ሌሎች ባለሀብቶችም ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረግን መዘንጋት የለባቸውም ነው ያሉት።

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው ፋውንዴሽኑ ማኅበራዊ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ግንባታዎቹም በራሳቸው ተቋራጭ በመገንባታቸው ጥራት ያላቸው ቤቶችን መኾናቸውን ነው የገለጹት። በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለፉት አራት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለማኅበራዊ አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት።

ለአቅመ ደካሞች ወርሃዊ ገንዘብ በመስጠት እና የጤና መድኅን ተጠቃሚ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ መጻሐፍትን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እየገነቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ግሩፑ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ከትርፍና ከንግድ በላይ አድርጎ የሚሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአማራ ክልል ድጋፍ በተጠየቀበት ሁሉ እየደረሰ ነው ብለዋል።

ግሩፑ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በነፃ ያስተማረችንን ሀገር ውለታ ለመመለስ የተማርንባቸውን ትምህርት ቤቶች መደገፍ ያስፈልጋል” አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ
Next articleበፍኖተ ሰላም ከተማ በ157 ሚሊዮን ብር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች እየተመረቁ ነው።