“በነፃ ያስተማረችንን ሀገር ውለታ ለመመለስ የተማርንባቸውን ትምህርት ቤቶች መደገፍ ያስፈልጋል” አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ

41

ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በነፃ ያስተማረችንን ሀገር ውለታ በማሰብ የተማርንባቸውን ትምህርት ቤቶች መደገፍና ማስዋብ ያስፈልጋል ሲል አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ተናገረ። አርቲስቱ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻያ ንቅናቄው ላይ ተሳታፊ እንዲሆንም ጥሪውን አቅርቧል።

አርቲስት ዘለቀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገረው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው “ትምህርት ለትውልድ” ሀገራዊ ንቅናቄ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዚህ አጋጣሚም በነፃ ያስተማረችንን ሀገር ውለታ በማሰብ የተማርንባቸውን ትምህርት ቤቶች በመደገፍ ደረጃቸውን ማሻሻል ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ሀገር በነፃ ነው ያስተማረችን ያለው አርቲስት ዘለቀ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የተማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች ክፍተት ለመሙላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነው የተናገረው።

እንደ አርቲስት ዘለቀ ገለጻ፤ ሁሉም ሰው የተማረበትን ትምህርት ቤት ወደ ኋላ ተመልሶ ቢያይና የአቅሙን ያህል የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ቢያደርግ ተደማምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ከ20 ዓመታት በላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና የትምህርት ግብዓቶችን ድጋፍ በማድረግ ማሳለፉን የገለጸው አርቲስት ዘለቀ፤ በዚህ የሥራ ሂደት ውስጥም አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የቁሳቁስና መሰል ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን መታዘብ መቻሉን ነው የገለጸው።

ትልቅ ቦታ ስንደርስ መለስ ብሎ ትናንት የተማሩበትን ትምህርት ቤት ምን ጎደለው ብሎ ለማሟላት መሥራት በትምህርት ጥራትም ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል አርቲስት ዘለቀ ገልጿል።

በገጠር አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው አስፈላጊ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው ናቸው ያለው አርቲስት ዘለቀ፤ በአንድ ክፍል ብዙ ተማሪዎች መማራቸው በትምህርት ጥራትና በተማሪዎች የመማር መስተማር ሂደት ውስጥ የሚኖረው ጫናም ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ንቅናቄ ሙሉ በሙሉ መንግሥት ላይ ቢተው ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ የተናገረው አርቲስት ዘለቀ፤ ታዋቂ ሰዎችንም ጨምሮ ሁሉም የማኅበረሰቡ አባላት ተሳታፊ መሆናቸው አስፈላጊ ነው ብሏል።

ተማሪዎች አብረው ከተማሯቸው ተማሪዎች ጋር ቢያንስ በወር አንዴ በመገናኘት አንድ መጽሐፍ እንኳን በማሰባሰብ መደገፍ ቢቻል ትልቅ ለውጥ ማምጣት ስለመቻሉም ነው አርቲስት ዘለቀ የተናገረው።

አርቲስት ዘለቀ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻያ ንቅናቄው የሕዝብን ትብብር እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን፤ የየወረዳ ትምህርት ቢሮዎችን ማጠናከር እንደሚገባ በማመላከት የተለያዩ የወላጅ ኮሚቴን በማቋቋም ሕዝቡ የራስነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ያስፈልጋልም ብሏል።

በትምህርት ቤቶች ከሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች መካከልም፣ የመመሪያ ህንጻ መፈራረስ፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እጥረት፣ የመጸዳጃ ቤት አለመኖር፣ ኤሌክትሪክ እንዲሁም የትምህርት ግብዓት እጥረት በዋናነት ይጠቀሳሉ።ንቅናቄው በዋናነት ያስፈለገውም እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየላሊበላ ቅርስ በተመረጡ 22 ቦታዎች አስቸኳይ የጥገና ሥራ እየተካሄደለት ነው።
Next articleበላይነህ ክንዴ ፋንውዴሽን በፍኖተ ሰላም ከተማ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለኾኑ ወገኖች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ።