የላሊበላ ቅርስ በተመረጡ 22 ቦታዎች አስቸኳይ የጥገና ሥራ እየተካሄደለት ነው።

31

ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የላሊበላ ቅርስ በተመረጡ 22 ቦታዎች ላይ አስቸኳይ የጥገና ሥራ እየተካሄደለት እንደሚገኘ የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ። የላሊበላ ቅርስ ጥገና ቢጀመርም በተያዘለት ጊዜ እንደማይጠናቀቅ የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የላሊበላ ቅርስ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ጥገናዎች እየተደረገለት ይገኛል። አንደኛው ጥገና “ዘላቂ ላሊበላ” በሚል ፕሮጀክት የሚደረግ ሲሆን፤ በቅርሱ በተመረጡ 22 ቦታዎች ላይ አስቸኳይ የጥገና ሥራ እየተካሄደለት ይገኛል።

ጥገናው ከ 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ጥገናም በ2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የወለል ሥራ ብቻ ቀርቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው ቅርሱን በማይጎዳና የተሻለ አገልግሎት በሚሰጥበት መንገድ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አያሌው ቦታውን ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ፣ ድልድይና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራም እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ሁለተኛው ጥገና አሁን ያለው መጠለያ በሌላ መጠለያ የመተካት ሥራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ጥገና ለማድረግ ከ2011 ዓ.ም ክረምት ጀምሮ በዩኔስኮ የተጠየቁ 12 ጥናቶች ሲሠሩ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገለጻ፤ ጥገናዎቹ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ በፈረንሳይና በኢትዮጵያ ባለሙያዎች የሚሰሩ ናቸው።

የላሊበላ ቅርስ ጥገና ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ሂደቱ ቆሞ እንደነበር አውስተው፤ይህም ለጥገናው መዘግየት እንደ ምክንያትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል። በዚህ ሳቢያም በ2018 ዓ.ም ጥገናው እንዲጠናቀቅ የጊዜ ገደብ ተቀምጦለት የነበረ ቢሆንም ከተቀመጠለት ጊዜ ሊዘገይ እንደሚችል ገልጸዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው የመጠለያው ዲዛይን በ2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ አመልክተው፤ዲዛይኑ እንደተሰራ የመጠለያው ሥራ ለጨረታ ክፍት ይደረጋል ብለዋል።

በቅርሱ ላይ ሊሰራ የታቀደው መጠለያ ከ 50 እስከ 70 ዓመታት ሊቆይ የሚችል መሆኑን ገልጸው፤ የሚወስደው ጊዜ ረዘም ያለ መሆኑ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል።

የሚሰራው መጠለያ ሁሉንም የላሊበላ አብያተ ቤተክርስትያናት በቡድን የሚያለብስ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ በሶስት ቡድኖችም ተከፍሎ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ቡድን ቤተማርያምና ቤተ መድኃኔዓለምን አንድ ላይ ሁለተኛው መጠለያ ቤተ አማኑኤል ፣ቤተ መርቆሪዮስን እስከ ቤተ ገብርኤል፤ ሦስተኛው መጠለያ ደግሞ ቤተ ጊዮርጊስን የሚያለብስ ተንቀሳቃሽ መጠለያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ መጠለያዎቹ ከቅርሱ ጋር ያላቸው ተዛምዶ፣ተጽእኖ እና ግብዓቱ ምንድነው የሚለው በጥንቃቄ ታይቶ የሚሠራ መሆኑን አንስተው፤ ለቅርሱ ስጋት የሚፈጥር እንዳይሆንም ትልቅ ጥንቃቄ ይደረጋል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት ያደረግነው የቢኩሎ ዓባይ የኮንክሪት ድልድይ ጠቀሚታው የላቀ ነው ” አቶ ሙሐመድ ያሲን
Next article“በነፃ ያስተማረችንን ሀገር ውለታ ለመመለስ የተማርንባቸውን ትምህርት ቤቶች መደገፍ ያስፈልጋል” አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ