ኢዜማ ከ400 በላይ ወረዳዎችን ያካተተ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

639

የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ አባላቶቹና የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርጓል። የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይና በፓርቲው ፖለቲካዊ ፕሮግራም ዙሪያ ነው ውይይቱን ያደረገው።

ኢዜማ በየትኛወም የሀገሪቱ ሕዝቦች የትኛውንም ቋንቋ፣ ባህልና እሴት ቢኖራቸም እንደ ዜጋ በእኩልነት የማስተናገድ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ አንደሚገኝ ተነግሯል። የዜጎች ማኅበራዊና ፍትሕ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየታተረ እንደሚገኝም የሚገልፅ ሐሳብ ለውይይቱ መነሻ ቀርቧል።

‹‹ፓርቲው የሀገሪቱን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ምን አስቧል? በመጭው ምርጫ ተወዳዳሪ ለመሆን ምን እየሠራ ነው? ሠላማዊ ምርጫ እንዲኖር ለአባላት ግንዛቤ መፈጠር አለበት?›› የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ከፓርቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች መልስ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የፓርቲው ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋ በሀገሪቱ የሚታዩት አለመረጋጋትና አደገኛ አካሄዶች የተፈጠሩት ከዜግነት ፖለቲካ ውጭ ሲደረጉ በነበሩ የዘር ፖለቲካ ሥርዓት የተፈጠሩ እንደሆኑና ከእንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት መውጣት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

‹‹ኢዜማ በዘር ሳይሆን ዜግነትን መሠረት ያደረገ፣ የሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችል የፖሊሲ አማራጭ ይዞ የመጣ ፓርቲ ነው›› ብለዋል አቶ የሺዋስ።

ፓርቲው በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የቆዩ አካላት የመሠረቱት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነና በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ብቁ ሆኖ ለመቅረብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር ጫኔ ከበደ (ዶክተር) ደግሞ የአባላቱን ቁጥር ለማብዛትና በምርጫው የተሻለ ድምፅ ለማግኘት ባለፉት ስድስት ወራት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱ ተናግረዋል። በመላ ሀገሪቱ በ408 የምርጫ ወረዳዎች አድማሱን እንዳሰፋም ነው ያስረዱት።

ፓርቲው ‹‹በአማራ ክልል 137 ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልል 83 ወረዳዎች፣ በትግራይ ክልል 37 ወረዳዎችን አካልሎ እየሠራ ይገኛል›› ተብሏል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ እንዲሆን ኢዜማ የሚገባውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

መጭው ምርጫ ውጤታማ እንዲሆን ሠላምና መረጋጋት መረጋገጥ እንዳለበት፣ ‹ለውጥ› የሚባለው ተቋማዊ መሆን እንደሚገባውና የፍትሕ ተቋማት ነፃነት፣ የሚድያና ሌሎችም አካላት ሙያዊ ኃላፊነት መከር እንዳለበትና በሐሳብ የበላይነት ወይም አማራጭ ፖሊሲዎች ተጠናክረው የሚመጡ ፓርቲዎች ቁጥር መበራከት እንለበት የፓርቲው እምነት መሆኑም ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

Previous articleበቀን 600 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታው ተጀመረ፡፡
Next articleበዋሽንግተን ዲሲ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀት ነገ ይቋቋማል፡፡