
ፋብሪካው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተማዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው።
500 ሜትሪክ ቶን የቅባት እህል አቀነባብሮ 600 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርት ‹ሸገር የምግብ ዘይት ፋብሪካ› በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ግንባታው ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር)፣ የኦሮሚያ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ጫልቱ ሳኒ እና የከተማ አመሥተዳድሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም በተገኙበት ነው የፋብሪካው ግንባታ ዛሬ የተጀመረው፡፡
በአራት ቢሊዮን ብር ግንባታው የሚከናወነው ይህ የምግብ ዘይት ፋብሪካ በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር) የከተማ አሥተዳደሩ ዋና ተግባር የከተማዋን ነዋሪ ሕይወት መቀየር መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ‹‹በተለይም የከተማዋን ነዋሪ እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር ማቅለል የከተማ አሥተዳድደሩ ዋነኛ ግብ ነው›› ብለዋል።
ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የዳቦ ፋብሪካና ግንባታው የተጀመረው የሸገር ዘይት ፋብሪካ የከተማ አስተዳድሩ ዕቅድና ፍላጎት ማሳያዎች እንደሆኑም አመላክተዋል።
ምንጭ፡- የአዲስ አበባ መሥተዳድር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት