ሁመራ የበርሃዋ ገነት፤ የይቅርታ እና ፍቅር ተምሳሌት!

57

ሁመራ: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አሁናዊው ሙቀቷ ክረምት ስለመሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ፀሐይ ያለገደብ ወጥታ ያለልክ ትሞቃለች፡፡ ታላቁን የተከዜ ወንዝ ተፈጥሯዊ ድንበር ተጠግታ የተመሰረተችው ጥንታዊት ከተማ እንደሙቀቷ ድምቀቷም ገራሚ የሚባል ነው፡፡ ከተከዜ ወንዝ የሚነሳው እና አልፎ አልፎ በዝግታ የሚነፍሰው ቅዝቃዜን ያዘለ ነፋስ አስደሳች ፋታ ይሰጣል፡፡ ተግባቢ እና ተጫዋች የሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች የበርሃዋን ሥር ከተማ ምድራዊ ገነት አድርገዋታል፡፡

ኢትዮጵያን ከኤርትራ እና ሱዳን ጋር በቅርብ ርቀት የምታዋስነው ሁመራ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መጥተው የሚዝናኑባት እና የሚኖሩባት ተመራጭ ከተማ እንደነበረች ይነገራል፡፡ ከአስመራ እስከ አዲስ አበባ፤ ከኦምናሃጀር እስከ ጎንደር እየተመላለሱ የሚነግዱ ሲራራ ነጋዴዎች የሚያርፉባት የበርሃዋ ገነት ሁመራ እንግዳን በፍቅር የመቀበል እና እንደባሕሉ የማባበል ልምድ አላት ይባልላታል፡፡

ትግርኛ ከኤርትራ ፤ አረብኛ ከሱዳን መጥተው በሕብር የሚነገሩባትና ሚደመጡባት የሰቲት መዲና አማርኛ አፍ መፍቻዋ ነው፡፡ በከተማዋ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቢኖሩም ፍቅር ግን የጋራ መግባቢያቸው ሆኗል፡፡ ሁመራ ውስጥ ሥራ ባሕል ነው፣ ትብብር መርህ ነው፣ መደጋገፍ እና መረዳዳት እሴት ነው፡፡ ሰርተው የሚበሉ እና ሰርተው የሚኖሩ የአዳም ዘሮች ሁሉ ልዩነት ሳይደረግባቸው በሰላም ወጥተው በሰላም ይገባሉ፡፡

በመኖሪያ ቤቶች እና በሆቴሎች በር ላይ ቅርንጫፎቻቸው የሰፉ ዛፎች ይበዛሉ፡፡ ከቤት ወጥተው በር አካባቢ ተቀምጠው ሻይ ቡና የሚያዘወትሩት ነዋሪዎች “ቤት ለእምቦሳ” የሚሏቸውን አላፊ አግዳሚዎች “እምቦሳ እሰሩ” ሲሉ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ነው፡፡ የሁመራ ሰዎች አዘውትረው የሚመገቡት ውጭ ላይ ተቀምጠው ነው፡፡ ውጭ ላይ የሚቆላው ቡና እና የሚጨሰው ጭሳጭስ ለከተማዋ ተወዳጅ ማዕዛን ሰጥቷታል፡፡

ፀሐይ ቀድማ ወጥታ ዘግይታ የምትገባባት ከተማ በተለይ ምሽት አካባቢ የተለየ የደስደስ አላት፡፡ በሁመራ ሰማይ ላይ የምትውለው ፀሐይ በምሽትም ብርሃኗ እንጂ ሙቀቷ ፈጽሞ አይቀንስም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን የበርሃዋ ገነት ከምሽት ጀምሮ ከእንደገና ነፍስ መዝራት ትጀምራለች፡፡ በአድማስ ጉያ ወደ ማደሪያዋ የምትገባዋን ፀሐይ ተከዜ ወንዝ ላይ ቆሞ መሸኘት የተለየ የሃሴት ድባብን ይፈጥራል፡፡

የሰቲቶች መዲና በየበርሃው እና በየጥላው ሥሩ የዋሉት ነዋሪዎቿ ለሽርሽር ብቅ የሚሉት የታፈነው አየር ለነፋሻማው ቦታ መልቀቅ ሲጀምር ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ፀጥ እረጭ ብለው የዋሉት አውራ ጎዳናዎች በሰው እና በተሽከርካሪ መጥለቅለቅ ይጀምራሉ፡፡ የቀኑን ንዳድ እና ሙቀት በአርምሞ የምታሳልፈው ከተማ ከምሽት ጀምሮ ነፍስ ይዘራባታል፡፡ በርሃ የዋሉት መዝናናት፤ ተዘግተው የዋሉት መሥራት የሚጀምሩት በዚህ ሰዓት ነው፡፡ ድንበር አልባው ሙዚቃ በተለያየ ቋንቋ በየምሽት ቤቶቹ በበርሃዋ ገነት ደምቆ ይደመጣል፡፡

ሁመራ አልፈው ለሚሄዱ እንግዶች ማደሪያ እና ከሌላ ቦታ ለሚመጡ ተመራጭ መኖሪያ ናት፡፡ ለሥራ መጥተው የለመዱ እና በሰፈራ መጥተው የተዋለዱ ኢትዮጵያዊያን ዘመንን እንደ ጅረት አሳልፈውባታል፡፡ በዘር፣ በብሔር እና በሃይማኖት መለያየት አብሮ ከመኖር ያላገዳቸው ነዋሪዎቿ ከዘመነ ወያኔ ጀምሮ ግን ሁመራ የኋላ ኪስ ሆነችባቸው፡፡ ታሪካዊው የተከዜ ድልድይ ለዓመታት ተዘግቶ ፍቅር በብሔር ግንብ ተከለለ፡፡ ሰፋሪዎች ባለርስቶችን በሚያሳደዱበት በዚሁ አካባቢ ሁመራ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ አስፈሪ እና አሳፋሪ የመረሳት ዘመንን አሳልፋለች ይላሉ ነዋሪዎቿ፡፡

1956 ዓ.ም ላይ ከትግራይ ክፍለ ሀገር አጋሜ አውራጃ አካባቢ እንደመጡ ያጫዎቱኝ አዛውንት አቶ ገብረ መድህን የእብዮ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ነዋሪነታቸውን በሁመራ ከተማ አድርገው ቆይተዋል፡፡ ስድስት ልጆችን ወልደው እና አሳድገው ለቁምነገር ያበቁት አባት ገብረ መድህን ከሁመራ ውጭ ሀገር እንደለሌለኝ እያሰብኩ አብዝቼ እወዳታለሁ ይላሉ፡፡ እትብቴ ባይቀበርባትም ዘላለማዊ እረፍቴ ግን ሁመራ እንደሚሆን አልጠራጠርም አሉኝ፡፡

“እኔ ስመጣ ሁመራ እና አካባቢው በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ወገራ አውራጃ ይተዳደር እንደነበር አስታውሳለሁ” የሚሉት አቶ ገብረ መድህን ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የተስተዋለው የደርግ መዳከም አካባቢውን የትግራይ ሰዎች እንዲቆጣጠሩት አድርጓል ይላሉ፡፡ በዘመኔ ሰርቶ ከማደር ያለፈ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ስላልነበረኝ ውስጠ ወይራውን ባላውቅም ሁመራ በተለይም በኤርትራ በኩል ያለው ድንበሯ ዝግ በመሆኑ ብዙ ነዋሪዎቿ ቅሬታ ነበራቸው ይላሉ፡፡ እንደ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልማቷ ባይካድም የተለያዩ አካባቢ ሰዎች እንደ ድሮው እየመጡ መሰባሰባቸው ግን እየቀነሰ መጣ፡፡

ወያኔ ባለፉት ዓመታት ከመንግሥት ጋር የፈጠረውን ቅራኔ ተከትሎ በተለይም በጦርነቱ ወቅት ሹመኞቹን ሲያሸሽ ሸሽተህ ቆይ ተብየ ነበር የሚሉት አቶ ገብረመድህን ከሁመራ ወጥቼ ወደየት እሸሻለሁ ብየ ነው የቀረሁ ብለውኛል፡፡ ጦርነት አውዳሚ በመሆኑ ያስፈራል፤ በወቅቱ ከተማዋ ውስጥ የነበረው ሁሉም ድባብ ያስፈራ ነበር፡፡ በሂደት ግን ያ ሁሉ አስፈሪ እና ጨለማ ጊዜ አልፎ የሰላም አየር ለማየት ብዙም አልፈጀም ነበር ይላሉ፡፡

ሁመራ ውስጥ ባሳለፍኳቸው 60 ዓመታት ውስጥ ከሥራ እና ሽምግልና የዘለለ ተሳትፎ ስላልነበረኝ ከማሕበረሰቡ ጋር ያለኝ መስተጋብር ጤናማ ነበር፡፡ አሁንም ቀድሞ ከማሳልፈው ሕይዎት የተለየ እና አስቸጋሪ የምለው ፈተና አልገጠመኝም የሚሉት አቶ ገብረመድህን የበርሃ ሰው ነገር ማሳደር አያውቅም፤ “ሁመራም የይቅርታ እና ፍቅር ተምሳሌት ናት” ይላሉ፡፡ ያለፈ አልፏል፤ ያለፈ ነገር ሲያስተምር ደግሞ ጥሩ ነውና ካለፈው መማር እንድንችል ልብ ይስጠን የዘዎትር ጸሎቴ ነው ብለውኛል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የከተማ ግብርና ሼዶችን ጎበኙ
Next articleበባቲ ከተማ አሥተዳደር ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።