በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በ128 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የመስኖ ፕሮጀክት ተመረቀ።

33

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በዳንግላ ወረዳ በ128 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ”ውምብሪ” የተሰኘ የመስኖ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቋል።
በምርቃቱ ላይ የክልልና የዞን አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአማራ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዳኝነት ፈንታ እንዳሉት የመስኖ ፕሮጀክቱ የክልሉን በመስኖ የማልማት አቅም የሚያሳድግ ነው።

ፕሮጀክቱ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ1 ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው ክልሉ በመስኖ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ278 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት 22 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ዘንድሮ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ የሚገቡ እንደ ”ውምብሪ” አይነት የመስኖ ፕሮጀክቶች በመስኖ የሚለማውን ማሳና የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም አሁን የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብአትና ለወጪ ንግድ የሚሆን በቂ ምርት ለማምረት እንደሚያግዝ ነው ያመለከቱት።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኘው በበኩላቸው ዞኑ ካለው በመስኖ የመልማት አቅም አንጻር እስካሁን ማልማት የተቻለው አነስተኛ የሚባል ነው ብለዋል።

በዞኑ ከ200 በላይ ትልልቅ ወንዞች ቢኖሩም እስካሁን ማልማት የተቻለው ከ31 ሺህ ሄክታር መሬት የማይበልጥ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል።

የ”ውምብሪ” የመስኖ ፕሮጀክት መጠናቀቅም በመጭው በጋ የሚለማውን ማሳ ከማሳደግ ባሻገር አርሶ አደሩ በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት ገቢውን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

📷 አዊ ኮሙኒኬሽን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሥራ ፈጣሪ እንጅ ሥራ ፈላጊ እንዳትኾኑ” የባምብ ኮሌጅ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት ጋሹ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የከተማ ግብርና ሼዶችን ጎበኙ