በአማራ ክልል የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች አያያዝ አሳሳቢ መሆኑ ተነገረ።

1218

በአማራ ክልል ከ4 ሺህ በላይ ቋሚና ከ130 ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዳሉ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ክልሉ የጥንት ኢትዮጵያውያን የኪነ ሕንጻ አሻራ ማስታወሻ የሆኑት የዓፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታት፣ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ የጣና ገዳማት፣ የጥሩሲና መስጂድና ሌሎችም ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤት ነው። የክርስትናም ይሁን የእስልምና ሃይማኖቶች፣ ሃይማኖታዊ ሚስጥርን ቋጥረው የያዙ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የብራና መጻሕፍትና ሌሎችም ደግሞ ክልሉ የያዛቸው ተንቀሳቃሽ አንጡራ ቅርሶች ናቸው።

ነገር ግን አብዛኞቹ ቅርሶች የተለያዩ አደጋዎች እንደተጋረጡባቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ የሚገኘው የደጅ አዝማች አያሌው ብሩ ቤተ መንግሥት በመፈራረስ ላይ ነው፤ ምንም ዓይነት ጥገና እየተደረገለት አለመሆኑንም ከወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ቤተ መንግሥቱ ስጋት ላይ መሆኑ እየታወቀ ምንም ዓይነት የጥገና በጀት እንዳልተያዘለትም ነው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰጠኝ አሌ ለአብመድ የተናገሩት።

በስጋት ሰንጠረዥ ውስጥ የሚገኘው ሌላኛው ቋሚ ቅርስ በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግሥት ነው። ቤተ መንግሥቱ በመፈራረስ ላይ እንደሚገኝ ከቦታው ድረስ ሄደን ታዝበናል።
በመርጡለ ማርያም ገዳም፣ በደሴ ባህል አምባ ኪነ ሕንጻ፣ በሰሜን ሸዋ ጎዜ መስጅድ … ተመሳሳይ አደጋዎች መጋረጣቸውን ከየአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። የላልይበላ፣ የጎንደር ወዘተ ኪነ ሕንጻዎች ያሉበት ደረጃ ጉዳይ በመገናኛ ብዙኃን ሲስተጋባ መስማት የዘወትር የጆሮ ቀለብ ከሆነም ሰነባብቷል።
ለመሆኑ የጉዳዩ ባለቤት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅርሶቹን ለመታደግ ምን እያከናወነ ይገኛል?

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳሬክተር ነህምያ አቤ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ክልሉ ካሉት በርካታ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች አንፃር ጥገናና እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚገኙት ጥቂቶች ናቸው። አብዛኞቹ ቋሚ ቅርሶች ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ ከመሆኑ አንፃር ጥገናውን በሁሉም አካባቢዎች ለማድረግ አዳጋች እንደሚያደረገው ተናግረዋል።

የበጀት እጥረት መኖርና ቅርሶቹ ታሪካዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ሊጠገኑባቸው የሚችሉ ጥሬ ዕቃዎች በበቂ ሁኔታ አለማግኘት የችግሮቹ መንስኤ ናቸውም ብለዋል።

ይሁን እንጅ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ቅርሶቹን የማዳን ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል። በሰጡት ማብራሪያም የክልሉ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ ለቅርሶች ጥገናና እንክብካቤ አውጥቷል። ይህም የፌዴራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣነ እያደረገ ካለው ድጋፍ ውጭ ነው። በዚህም ከ53 በላይ ታሪካዊ ቅርሶች ጥገና እንደተደረገላቸው ነው ዳሬክተሩ ያስረዱት። የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም፣ የግንብ ጊዮርጊስ፣ የጎዜ መስጅድ … ይገኙበታል። በዚህ በጀት ዓመት ጥገና ይደረግላቸዋል ተብለው ለተያዙት ደግሞ 7 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ያሉትን ተንቀሳቃሽ ታሪካዊ ቅርሶችን ከስርቆትና ከጉዳት ለመንከባከብ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ያሉትን ቅርሶች መዝግቦ መያዝ፣ ጥገና የሚደረግላቸው ታሪካዊነታቸውን እንዳይለቅቁ ለማድረግ ጥንቃቄ ማድረግና በቅርስ አያያዝ ዙሪያ ያለው የማኅበረሱ እሳቤ ማሳደግ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል እንደሆኑም ተጠቁሟል።

ሀገር በቀል የጥገና ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች አቅምና ቁጥር ለማሳደግም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ረህመት አደም

Previous articleመንግሥት ይከተለው የነበረውን የ70፡30 የተማሪዎች ምደባ ወደ 55፡45 ቀየረ፡፡
Next articleበቀን 600 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታው ተጀመረ፡፡