“ሥራ ፈጣሪ እንጅ ሥራ ፈላጊ እንዳትኾኑ” የባምብ ኮሌጅ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት ጋሹ

48

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባምባ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ባገኘባቸው አካውንቲንግ እና ፋይናንስ እንዲሁም ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 678 ተማሪዎች እያስመረቀ ነው።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 55 በመቶ ሴቶች ናቸው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ሥራ እና ሥል ጠና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ አማረ አለሙ፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል።

የኮሌጁ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት ጋሹ ለተመራቂዎች እና ለወላጆች እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሥራ አስኪያጁ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት መመረቅ የመጀመሪያ እንጅ የመጨረሻ ግብ አይደለም ብለዋል ተመራቂዎች ሥራ ፈጣሪ እንጅ ሥራ ፈላጊ እንዳይኾኑም አሳስበዋል።
ኮሌጁ በ2011 ዓ.ም ሥራ የጀመረ ሲኾን የበኩር ልጆችን ለቁምነገር አብቅቷል። ኮሌጁ አድማሱን አስፍቶ በሌሎች ክልሎች እና በሌሎች የትምህርት ዘርፎች ለመሳተፍ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ተማሪ ልዑል ሽመልስ በመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በአካውንቲንግ እና ፈይናንስ ትምህርት ክፍል በሁሉም የትምህርት ዓይነት “A” በማምጣት የኮሌጁ ተሸላሚ ተማሪ ነው። ተማሪ ልዑል በርትቶ በማጥናቱ ባገኘው ውጤት ደስተኛ መኾኑን ተናግሯል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሠጠው የመውጫ ፈተናም የተሻለ ውጤት ማምጣቱን ነው የነገረን። ተማሪ ልዑል ሙያውን በማሳደግ ሥራ ፈጣሪ ለመኾን ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል።

ሌላኛዋ የተሻለ ውጤት በማምጣት የተመረቀችው ተማሪ ፍሬህይወት አለሙ በተማረችበት የትምህርት ክፍል ሀገሯን በታማኝነት ለማገልገል ቃል መግባቷን ተናግራለች።

ያስተማሯት እና ለውጤት ያበቋትን የኮሌጁ መምህራን እና ሠራተኞች አመስግናለች። ተማሪ ፍሬሕይዎት አለሙ ከሴቶች 3 ነጥብ 96 ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ኾናለች።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወልድያ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በ128 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የመስኖ ፕሮጀክት ተመረቀ።