
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሐይላንድ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ተመስገን አበራ በምረቃ ሥነ ሥርዐቱ ላይ እንደተናገሩት ፣ሐይላንድ ኮሌጁ በዲግሪ ፕሮግራምና በቴክኒክና ሙያ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 376 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
✍ ከተመራቂዎች 357 ተማሪዎች በዲግሪ ፕሮግራም፣19 ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ነው የሰለጠኑት ተብሏል።
ኮሌጁ የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ እና ገበያው የሚፈልገውን ዘርፍ መሰረት አድርጎ የሰለጠነ የሰው ኀይል የማፍራት ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደኾነም የኮሌጁ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል።
ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክትም በተለይም መንግሥት ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሥራ ባለበት ወቅት መመዘኛዎችን ሁሉ አልፋችሁ ተመርቃችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
መማር የባሕሪ ለውጥ ማምጣት ነውና በሰለጠናችሁበት የትምህርት መስክ፣ ባገኛችሁት እውቀትና ክህሎት ሀገርና ሕዝባችሁን በታማኝነት፣በቅንነት እና በብቃት እንድታገለግሉ አደራ እላለሁ ነው ያሉት።
በምርቃ ሥነ ሥርዐቱ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ስልጠና መምሪያ ኀላፊ አስሜ ብርሌ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ ችግር ፈች ምርምሮችን ማድረግ ፣ የጥናትና ምርምር መድረክ በማዘጋጀት በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር አበርክቷል ብለዋል።
ትምህርት ለሀገር ግንባታ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘልቅ ነው የሚሉት አቶ አስሜ ለትምህርት ጥራት ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና በኀላፊነት መሥራትን የሚጠይቅ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት።
መምሪያ ኀላፊው አስሜ ብርሌ ለተመራቂዎቹ እንዳሉት የዛሬ ተመራቂዎች የሥራ ዘመንን ለመጀመር የመጀመሪያው በር ነው ያገኛችሁት ብለዋል።
በቀጣይ በቅጥርም ኾነ በሥራ ፈጠራ በምትቀላቀሉበት የሥራ መስክ ከራሳችሁ አልፎ ለሀገርና ለሕዝብ እድገት መሰረት ለመጣል ተዘጋጁ ሲሉ አሳስበዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተመራቂ ተማሪዎችም በሰለጠኑበት ሙያ እራሳቸውንም ወገኖቻቸውንም ለማገልገል ዝግጁ እንደኾኑ ነው የተናገሩት።
ከተመራቂዎች መካክል ተማሪ አበባው አለልኝ በማኔጅመንት የትምህርት መስክ በኮሌጁ በማዕረግ ለመመረቅ በቅቷል።
ተመራቂው እንደተናገረው ሀገር ከመቸውም ጊዜ በላይ በእውቀት እና በታማኝነት አገልጋይ ዜጋ የምትፈልግበት ወቅት ነው፣ እናም በሰለጠንኩበት ሙያ ሀገሬንና ወገኔን በታማኝነት አገለግላለሁ ነው ያለው።
ሌለዋ ተመራቂ ረድኤት ምኒልክ በበኩሏ ለዚህ ያበቋትን ቤተሰቦቿን አመሥግናለች፣በተማረችበት የትምህርት ዘርፍም በታማኝነት እንደምታገለግል ነው የተናገረችው።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!