“በሙያቸው ብቁና ተወዳዳሪ ሰልጣኞችን በማሰልጠን በሥራ ፈጠራ ራሳቸውን እና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎችን ለማፍራት እየሠራሁ ነው” የእንጅባራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ

42

እንጅባራ: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ21ኛ ጊዜ በ18 የሙያ መስኮች በደረጃ 4 እና 5 በመደበኛና በማታው መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን 298 ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡

👉 የእንጅባራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከተቋቋመበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጣኞችን አሰልጥኖ እያስመረቀ ይገኛል፡፡

👉 በዚህ ዓመትም ለ21ኛ ጊዜ 156 ሴትና 142 ወንድ ሰልጣኞችን ነው ያስመረቀው።

በምርቃት ሥነ ሥርዐቱ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ከእንጅባራ ከተማ አሥተዳደርና ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጥሪ የተደረገላቸው ባለሙያዎችና የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ታድመዋል፡፡

የእንጅባራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አስፈራው አጠና በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት ኮሌጃቸው የገበያ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ላጠናቀቁ ተማሪዎች በተለያዩ ሙያዎች ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት በመደበኛና በማታው መርሐ ግብር ስልጠና እየሰጠ ነው።

👉ኮሌጁ የሚሰጠው ስልጠና ሰልጣኞች በአመለካከት ፣ በክህሎትና በሙያ ብቁ ኾነው በመውጣት ሥራ ፈጣሪና ዘመናዊ ቴክኖሎጅን የሚያላምዱ፣ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የድርሻቸውን ሚና የሚወጡ እንዲኾኑ ያስችላቸዋል።

👉እንጅባራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከመደበኛው የስልጠና መርሐ ግብር በተጨማሪ በተለያዩ የሙያ መስኮች አጫጭር ስልጠና ለአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶች በመስጠት ለሥራ ብቁ እንዲኾኑ እየሠራ እንደሚገኝም የኮሌጁ ዲን ገልጸዋል፡፡

👉 ከኮሌጁ ተመራቂ ሰልጣኞች መካከል አማረች ፈንታሁንና ሀብታሙ ሙሉ ለአሚኮ እንዳሉት በኮሌጁ ቆይታቸው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን የሙያና የእውቀት ክህሎት ተጠቅመው የመንግሥት ሥራ ጠባቂ ሳይኾኑ ሥራ ፈጣሪ በመኾን ራሳቸውን እና ሀገርን ለመጥቀም የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ፡፡

ዘጋቢ፦ ግዛቸው ያረጋል

ፎቶ ፦ሙሉሰው ቦጋለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጦርነት የተጎዱ የውኃ ተቋማትን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን የደቡብ ወሎ ዞን ውኃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።
Next articleሐይላንድ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ370 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ።