
ደሴ: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ውኃና ኢነርጂ መምሪያ የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በደሴ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የደቡብ ወሎ ዞን ውኃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ፅጌ፤ በዞኑ በጦርነቱ ከ 1ነጥብ8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት በውኃ ተቋማት ላይ ደርሷል ።
በበጀት ዓመቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የውኃ ተቋማት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉ ተገልጿል ።
በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ከጦርነት በኋላ 56 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው የውኃ ሽፋን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ 66 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም አጋር ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል ።
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ተስፋዬ አባቡ በበኩላቸው በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት ከ 1 ሺህ 430 በላይ የውኃ ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል ። እነዚህን ተቋማት መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ለማብቃት ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ማኅበረሰቡም የውኃ ተቋማትን በባለቤትነት የመጠቀም ልምዱ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በመድረኩ የወረዳ አሥተዳዳሪዎች፣ የውኃና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ና የከተማ ውኃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ተሳታፊ ናቸው ።
ዘጋቢ:- ሰይድ አብዱ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!