
[ዝክረ ታሪክ – አቡነ ጴጥሮስ]
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ፍቅሯ ሞተዋልና ምድሯ ጴጥሮስ ጴጥሮስ ትላለች፣ ስለ ክብሯ መስዋዕት ኾነዋልና ስማቸውን እየደጋገመች ትጠራለች፣ ጴጥሮስ ሰማዕት እያለች ታከብራለች፣ ቃል ኪዳናቸውን ትጠብቃለች፣ ለልጆቿ ታስተምራለች፣ በማይጠፋ ቀለም፣ በማያረጅ ብራና ቀርጻ አስቀምጣለች፣ ዓመታት አልፈው ዓመታት ሲከተሉ ትዘክራቸዋለች፡፡
ኢትዮጵያን አብዝተው ወደዷት፣ ታላቅነቷን በጠላቶቿ ፊት መሰከሩላት፣ ነጻነቷን በደማቸው አጸኑላት፣ በገዳዮቻቸው ፊት እውነቷን ተናገሩላት፣ በሞት ፊት ኾነው ትውልድ ሁሉ ይጠብቃት ዘንድ ቃል ኪዳን አኖሩላት፣ እርሷን የሚክደውን ካዱት፣ እርሷን የሚወደውን ወደዱት፣ በቀና ልባቸው፣ አምላክ በመረጠው ብጽዕናቸው መረቁት፡፡ ሃይማኖታቸውን በርትተው ጠበቋት፣ ትዕዛዛቷን አከበሩላት፣ አክብረውም አስከበሩላት፡፡
የሀገር ፍቅራቸው ሞትን አስንቋቸዋል፣ የጥይት አረርን አስረስቷቸዋል፡፡ በሀገራቸው እና በሃይማኖታቸው የመጣባቸውን ጠላት ፊት ለፊት ታገሉት፣ ባሩድ የሚተፋ ጠመንጃ ይዞ እያስፈራራቸው ናቁት፣ መሳደድም ቢኾን፣ መሰቃየትም ቢኾን፣ መጠማትም ቢኾን፣ መራብም ቢኾን፣ መታሰርና መገረፍም ቢኾን፣ ሞትም ቢኾን ሃይማኖታቸውን፣ ሀገራቸውን እና ነጻነታቸውን ከመጠበቅ እንደማያቆማቸው ነገሩት፡፡
ጠላቶቻቸው ገድለው ነጻነታቸውን፣ ሃይማኖታቸውን እና ሀገራቸውን አሳጣናቸው ሲሉ እርሳቸው ግን በሞታቸው አሸነፏቸው፣ በቃል ኪዳናቸው ድል መቷቸው፣ እረኛውን ገደልን በጎችን በተናቸው ሲሉ እርሳቸው ግን በሞታቸው በጎቻቸውን ሰበሰቧቸው፣ በቃል ኪዳናቸው አንድ አደረጓቸው፣ ከዳር እስከ ዳር አሰባሰቧቸው፣ በቃል ኪዳን፣ በግዝት አስረው ለሀገራቸው ነጻነት አስነሷቸው፡፡ በሞታቸው ገዳዮችን ድል መትተዋል፣ እስከ ሞት ድረስ በታመነው የሀገር ፍቅራቸው ነጻነትን አምጥተዋል፣ ሕዝብን አንድ አድርገዋል፡፡ አርበኞችን በእልህና በወኔ አስነስተዋል፡፡
“ ለአረበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው” የተባለውም ለዚያ ነው፡፡
አምላክ የመረጣቸው ብጹዕ ናቸው፡፡ ትውልድ ሁሉ የሚወዳቸው፣ የሚመካባቸው ሰማዕት ናቸው፡፡ መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንዕነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒትነ ነፍስነ እያሉ መስቀል ብቻ ጨብጠው ከጠላት ጋር የተዋጉ አርበኛም ናቸው፡፡ ረቂቁን የሚያነጥሩ፣ ምስጢር የሚያሜሰጥሩ ሊቅ ናቸው፡፡ ከበጎቻቸው በፊት የሚቀድሙ፣ ስለ ፍቅር ለመስዋዕት የቀረቡ ጀግና ታማኝ እረኛም ናቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፡፡
ዓድዋ ላይ እንደ ዱቄት የተበተነችው፣ በኃያል ክንድ የደቀቀችው፣ ከሮም ተጉዛ በኢትዮጵያ ተራራዎች ለኢትዮጵያ የሰገደችው፣ ፎክራ መጥታ አልቅሳ የተመለሰችው፣ ንቃ መጥታ የተዋረደችው፣ ክብር አዋርዳለሁ፣ ነጻነት እገፍፋለሁ፣ ሀገር አሳጣለሁ ስትል በብርቱ ጀግኖች የተዋረደችው ኢጣልያ ከአርባ ዓመታት በኋላ ለበቀል መጥታ ነበር፡፡ በአምባላጌ፣ በመቀሌና በዓድዋ ላይ ደማቸው የፈሰሰባትን፣ አጥንታቸው የተከሰከሰባትን ልጆቿ ደም ልትመልስላቸው፣ የጣለችውን ክብሯን ልታነሳው፣ ውርደቷን ልትክሰው ዳግም ከሮም ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡
በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አባ ዳኛው ምኒልክ አልፈው፣ አባ ጠቅል ኃይለ ሥላሴ ነግሰዋል፡፡ አባ ጠቅል ኃይለ ሥላሴ ለዙፋን ያበቃቸውን አምላካቸውን እያመሰገኑ ከአባቶቻቸው የተረከቧትን ሀገር ነጻነቷን፣ ክብሯን እና ታሪኳን ጠብቀው ለማኖር ደፋ ቀና ላይ ናቸው፡፡ ኢጣልያ ግን በአባ ዳኛው ዘመን የደረሰባትን ሽንፈት በእርሳቸው ዘመን ልታካክስ ሀገራቸውን ወጋችባቸው፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም አልደረስንባችሁም፣ አትድረሱብን፣ ተውን አሏቸው፡፡ ኢጣልያ አሻፈረኝ አለች፡፡ ሀገራቸውንም ወረረች፡፡
ንጉሡ ያቀረቡት የሰላምና የፍቅር ጥሪ ሰሚ አጣ፡፡ በኃይል የመጣውን ወራሪ በኃይል ለመመለስ የሀገራቸውን ጀግኖች ሰበሰቡ፡፡ እሳቸውም ዘመቱ፡፡ እርሳቸው ወደ ማይጨው ሲዘምቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም አብረው ዘምተው ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው የሀገራቸውን ጀግኖች በጸሎት እያበረቱ፣ አምላካቸው ሀገራቸውን እንዲጠብቅላቸው እየተማጸኑ ነበር ወደ ማይጨው ያቀኑት፡፡ ጠላት አብያተክርስቲያናትን እያቃጠለ፣ ካህናትን እየገደለ፣ ምዕመናንን በመርዝ እያሰቃየ ነበርና እረኛው እኔም ለበጎቼና ለሀገሬ እዘምታለሁ ብለው ዘመቱ፡፡
ኢጣልያ ለአርባ ዓመታት የተዘጋጀችበት፣ መርዝና የዘመኑ መሣሪያዎችን የታጠቀችበት ጦርነት ነበርና እንደ ዓድዋው ዘመን ሁሉ በቶሎ ድል መምታት አልተቻለም፡፡ ጦርነቱ ጊዜ ይወስድ ነበር፡፡ ንጉሡ ወደ ዙፋናቸው መቀመጫ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖችም በዱር በገደሉ ከጠላት ጋር መፋለማቸውን ቀጠሉ፡፡ ጦርነቱ በዱር በገደሉ ቀጠለ፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም ሀገራቸውን ላለማስደፈር የሚዋደቁትን ጀግኖች ያበረታቷቸዋል፣ ያለ ድካም ይጸልዩላቸዋል፡፡
ጦርነት ቀጠለ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከማይጨው ከተመለሱ በኋላ ሚያዚያ 24 ቀን ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከዚያም ኾነው የሰላሌን አርበኞች በስብከት ያነቃቁ ጀመር፡፡ በዚህም ለኢጣልያ የገቡና በኢጣልያ አገዛዝ ያመኑ የኢትዮጵያ ቀሳውስት አቡነ ጴጥሮስ ለኢጣልያ እንዲገቡና በኢጣልያ ላይ የሚነዙትን አጉል ስብከት እንዲተዉ በደብዳቤም በቃልም ይመክሯቸው ጀመር፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ግን ማንኛውንም ልመና አልተቀበሉትም ብለዋል፡፡
የእሳቸው ሃሳብና ተግባር እውነት ነበር እንጂ አጉል አልነበረምና እንዲያስተዋቸው ለሚጠይቃቸው ሁሉ ጀሮ አልሰጡትም፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች በየቀኑ የዙፋን መቀመጫዋን አዲስ አበባን ለማስለቀቅ ይዋጋሉ፡፡ የኢጣልያ ሠራዊትም ይሸበራል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ፓትሪክ ሮበርትስንን ጠቅሰው ሲጽፉ “ ኢትዮጵያውያኖች የሚያስገርምና ከባድ ውጊያም አደረጉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጠጉ ሲሄዱም ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ ሲገቡ የኢጣልያ ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያውያኖቹ ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሱ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ከተማዋ ድረስ ከአርበኞቹ ጋር አብረው የመጡ ናቸው፡፡ የተያዙትም በጦርነቱ ውስጥ ነው” ብሏል በማለት ጽፈዋል፡፡
ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ “ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አርበኞች ከአዲስ አበባ ሲመለሱ እሳቸው ግን የአዲስ አበባ ከተማን ትተው ለመሄድ አልፈቀዱም፡፡ በመኾኑም ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርጋለሁ ካልኾነ ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላ ከተማዋ ባሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች መካከል ብፁዕነታቸው እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ አልቻሉም፡፡ በዚሁ በከተማም ተሰውሬ መኖር አልፈልግም ወደገጠርም ፊቴን አልመልስም በማለት ለኢጣልያ እንደራሴ እጃቸውን ሰጡ፡፡ የኢጣልያ እንደራሴም ወዲያው ለግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸው ” ብለዋል፡፡ የኢጣልያ እንደራሴ የነበሩትም ኢትዮጵያዊ ሰው ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽሽቶች እጅ ከገቡ በኋላ ሞት ተፈረደባቸው፡፡ ብፁዕ ኾነው ሳለ እንደ በደለኛ ሞት ተፈረደባቸው፣ ሃይማኖት ጠባቂ፣ የሀገር ፍቅር አዋቂ ኾነው ሳለ ይገደሉ ተባሉ፡፡ ሀገሬን አትንኩ፣ ሃይማኖቴን አትዳፈሩ ባሉ እንደ ሀጥያተኛ ተቆጠሩ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኮሪየር ዴላ ሤራ ጋዜጠኛ የነበረውን ፓጃሊን ጠቅሰው ሲጽፉ “ በጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ፡፡ ይህ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ተፈጠረ፡፡ ጉዳዮም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ” ብለዋል፡፡
ፍርዱ ተፈረደ፡፡ ጳጳሱ ከሞት ደጅ፣ ከገዳዮች ፊት ቆሙ፡፡ ከሳሾቻቸውና ፈራጆቻቸው ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍ “ ካህናቱም ኾኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ኾኑ ? ሲል ጠየቃቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስም መለሱ፡፡ አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኀላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡
ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ” ማለታቸው ተጽፏል፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ወደ መግደያው ሥፍራ ተወሰዱ፡፡ እጅግ የከበረውን፣ ትውልድን ከትውልድ ጋር የሚያስተሳስረውን፣ ዘመናትን አልፎ የሚሰማውን ቃል ከአንደበታቸው አወጡ፡፡ “ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ ፋሽሽቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣልያ ፋሽሽት ነው፡፡ አረማዊ የኾነው የፋሽሽት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡፡ በጎ ለመሥራት እውነተኛ ለመፍረድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሞታችሁ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፡፡
የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን” አሉ፡፡
አቡነ ጴጥሮስን ገድለው ክብር ማግኘት የሚሹ ገዳዮች ለመግደል አኮበኮቡ፡፡ ከአቡነ ጴጥሮስ ሃያ እርምጃ ያክል ርቀው በርከክ አሉ፡፡ በአስተኳሹ ትዕዛዝም ተኮሱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ጀርባቸው ላይ ተተኮሰባቸውና ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ አልሞቱም ነበርና በድጋሜ በሦስት ጥይት ራሳቸውን ተመትተው ተገደሉ፡፡ ታላቁ አባት በሰማዕትነት ያረፉባት ቀንም ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበረች፡፡ ታማኙ እረኛ በጽኑ እምነት አለፉ፡፡ የእርሳቸውን ሞት የሰሙ ሁሉ አባታችን እያሉ አለቀሱ፡፡ አርበኞችም የታላቁ አባት መስዋዕትነት ወኔ እየኾናቸው ለነጻነት ለመሞት ቆረጡ፡፡
“ እንደዚህ ነው ክህነት ዘመንን መቀደስ
በደምና በአጥንት ጽኑ ሀገር ማውረስ” በደምና በአጥንታቸው ጽኑ ሀገር አወረሱ፡፡ በጽኑ ታማኝነታቸው አርበኞችን አጸኑ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለሠንደቃቸው፣ ለነጻነታቸው፣ ለክብራቸው እንዲዋደቁ አደረጓቸው፡፡ በሞታቸው ጠላትን ድል መቱት፡፡ በታማኝነታቸው ዘመንን ቀደሱት፡፡ ዘመንን የቀደሱ፣ ጽኑ ሀገር ያወረሱ አባት ሆይ ክብር ይገባዎታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!