
ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ተደጋጋሚ ጉዳቶችና የሜዳ ላይ አቋም መቀነስ እግር ኳስ እንዳቆም አስገድደውኛል ሲል አንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ሰይድ ተናገረ፡፡
ሳላዲን እግር ኳስ የማቆሙ ዜና ከተሰማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
እግርኳስ ያቆመበትን ምክንያት ያስረዳው ሳላዲን ከጉዳት ጋር በሚያጋጥመው የጤና እክሎች እና በቆይታው ምክንያት ባሳየው ደካማ አቋም ምክንያት እግር ኳስ ለማቆም መወሰኑን አብራርቷል፡፡
በቀጣይ እረፍት ለማድረግና ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ እቅድ መያዙን፣ ከእረፍት መልስ ደግሞ በእግርኳስ ውስጥ ባሉ ዘርፎች ሊሰማራ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
ከሀገር ውጭ በተለያዩ ሀገራት ሊጎች የመጫውት ዕድል የነበረው ሳላዲን÷ በተጫዋች ደረጃ ከኛ ሀገር ጋር ሲነፃፀር ምንም ልዩነት የለም ብሏል።
ልዩነቱ በሌሎች ሀገራት ትኩረት የተሰጠው የእግር ኳስ ዘርፍ በኛ ሀገር ትኩረት አለማግኘቱ ብቻ ነው በማለት ገልጿል።
ሳላዲን በአጥቂ ደረጃ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ እንዲሁም ከመሐል ክፍል ደግሞ የአሸናፊ ግርማ እና ሙሉዓለም ረጋሳ አድናቂ መኾኑን ተናግሯል፡፡
በመጨረሻም በስኬታማ የእግር ኳስ ህይወቱ አስተዋፅዖ ላደረጉለት አሰልጣኞች፣ የብሔራዊ ቡድን እና የክለብ አጋሮቹ እንዲሁም ለመላው የእግርኳስ ቤተሰብ እና ደጋፊዎች ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!