ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በሀገርና ክልል አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ አበዳሪ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ፊርማ አካሂዷል፡፡ ስምምነቱ በክልሉ በሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ሥራ (ካዳስተር) በተሠራባቸው እና እየተሠራባቸው በሚገኙ የክልሉ አካባቢዎች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ዋስትና በማስያዝ የብደር ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ በክልሉ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ ደብተር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ከ711 ሚሊዮን ብር በላይ የሁለተኛ ደረጃ ደብተራቸውን ዋስትና አስይዘው የብድር ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል፡፡
በዛሬው እለትም አርሶ አደሮቹ በሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ ደብተር ዋስትና የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ ከ10 በላይ አበዳሪ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የግብርና ግብዓትና የቴክኖሎጅ ውጤቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እና በራሳቸው ገዝተው እንዲጠቀሙ ያግዛል ተብሏል፡፡
ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ በሌሎች የኢኮኖሚ አመንጭ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉም ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥር አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ብድር አቅርቦት ለማሳደግ ከሁሉም ባንኮች ጋር ውል ለመውሰድ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የ”ፒስ ማይክሮ ፋይናንስ” ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተዘራ ከበደ እንዳሉት አርሶ አደሮች በመሬት ማረጋገጫ ደብተር ብድር ማግኘታቸው ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ግብዓቶችን በፈለጉት ጊዜ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
የመክሊት ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘገየ ባንቲ እንዳሉት ደግሞ ለአርሶ አደሮች በተናጠል በመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ብድር እንዲያገኙ መደረጉ ከግብርና ባለፈ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም እንዲያከናውኑ እድል ፈጥሯል፡፡ ይህም አርሶ አደሩን ብቻ ሳይኾን አበዳሪ ተቋማትንም ውጤታማ ማድረጉን አንስተዋል፡፡ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የሚደረገው የብድር አቅርቦት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አበዳሪ ተቋማት ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!