
ሁመራ: ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወልቃይት ገብቼ ደጀና ላይ ወጣሁ፡፡ ጭርቆስ ማይ ለመሞን አየሁት፤ እንኳን ታሪኩ ተጭኖት ደብሩ ብቻውን ያስፈራል፡፡ ፈሪ ስትሆን አስፈሪ ነገር ፍጽሞ አትወድም፡፡
ወያኔ ከወልቃይት ምድር ደጀናን በተለይም ደግሞ ጭርቆስ ማይ ለመሞን አብዝቶ አይወደውም ነበር ይባላል፡፡ ወያኔዎች ከደጀና ከመጣ ሴት እና መነኩሴ እንኳን ቢሆን ያስሩ ነበር አሉ፡፡ የፈሩት ይደርሳል ሆነና ነገሩ ደጀናዎች ወያኔን ከላይ ከደጋው ተቀብለው ወደ ታች በርሃውን አሳልፈው ተከዜን አሻገሩት፡፡
ደጀናዎች እንኳን ጸባቸው ፍቅራቸውም ያስጨንቃል ይሏቸዋል፡፡ “ጭርቆስ ማይ ለመሞ የሁለት ፈሪ ሀገር፤ ወይ እነርሱ አይመጡ ወይ እኛ አንሻገር” እንዳሉ ገሪማ ታፈረ በመጽሐፋቸው፡፡ ለአባ አለነ አበራ ይኽችን ግጥም ሳነሳላቸው ለዛ ባለው የሽምግልና ፊታቸው ላይ እንደጨረቃ የሚደምቅ፤ እንደ ፀሐይ የሚሞቅ ፈገግታ ብልጭ አድርገውልኝ “አልሰማህም እንዴ፤ ተሻግረን አሻገርናቸው እኮ” አሉኝ እየሳቁ፡፡
ከልጅነት እስከ እውቀት ያለው የ86 ዓመታት የአባ አለነ አበራ ሕይዎት ደጀና ላይ ተጀምሮ ደጀና ላይ የፀና ነው፡፡ ጭርቆስ ማይ ለመሞን ደግሞ ከተማሪነት እስከ አስተዳዳሪነት ያሉትን የትምህርት እና የኅላፊነት ቦታዎች ሁሉ አሳልፈውበታል፡፡ ደብሩ እና አባ አለነ ቁርኝታቸው የጠበቀ ይመስላል፡፡ ደብሩን ሲነኩባቸው፤ ቤተ ክርስቲያኑን ሲዳፈሩባቸው ያማቸዋል፡፡ ከወያኔ ጋር ያላቸው ቅራኔ የተመሰረተውም ከጭርቆስ ማይ ለመሞ ጋር በተገናኘ ነው ብለውኛል፡፡
ወያኔዎች በባህሪያቸው ሃይማኖት ለመጣስ፣ ቤተ ክርስቲያን ለመዳፈር፣ ትልቅ ለማዋረድ እና ሀገር ለመናድ የተፈጠሩ እስኪመስሉ ድረስ ከልማት እስከ ጥፋት ያላቸው ሂደት ከዚህ አያልፍም ይላሉ፡፡ ከዳንሻ እና ከማክሰኞ ገበያ ያመጡት አውራ ጎዳና ጭርቆስ ማይ ለመሞን ነክቶ ነው የሚያልፈው የሚሉት አባ አለነ ለቤተ ክርስቲያኑ 460 ሺህ ብር ካሳ ተፈቅዶለት ወያኔዎች በሉት ይላሉ አሁንም ድረስ በብስጭት፡፡
የቤተ ክርስቲያኑን የካሳ ገንዘብ ለማስመለስ ከወያኔ ሹመኞች ጋር አንገት ለአንገት የተናነቁት አባት የመጨረሻ እጣ ፋንታቸው ለእስር መዳረግ ኾነ፡፡ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በቀደሱበት ደብር እና ወንበር ዘርግተው ባስተማሩበት ሀገር “እናንተን መሰሎች እያላችሁ ሀገር ሰላም አትኾንም” እየተባሉ ተንገላቱ፡፡ አባ አለነ እስር ላይ እያሉ ሊጠይቋቸው የሚመጡት እየተንገራገሩ እና ዋሳቸው እንሁን የሚሉት እየተስፈራሩ ከተመለሱ በኋላ ደስ ባላቸው ጊዜ ከእለታት በአንዱ ቀን ከእስር ተፈትተዋልና ይውጡ ተባሉ፡፡ ጥፋቴን ሳላውቅ፤ ከሕግ ሳልቀርብ አልፈታም ማለታቸውን ተከትሎ እንኳን ክህነት ተጨምሮ እድሜ ብቻ የሚሰጣቸውን ክብር ተነፍገው ተንገላተዋል፡፡
አባ አለነ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ወያኔዎች አዘናግተው አካባቢውን እስኪቆጣጠሩት ድረስ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ እርስት ስለመኾኑ ፊት ለፊት ስለሚናገሩ አይወዷቸውም ነበር፡፡ ይኽ ጥላቻ ደግሞ እስከ ልጆቻቸው ድረስ ወርዶ ቤተሰቡን ሁሉ መከራ አብልቶታል፡፡ ሃይማኖት እና ሀገር ለድርድር አይቀርቡም የሚሉት አባ አለነ “ጅብ ከሚበላህ ጅብ በልተህ ተቀደስ” ይላሉ፡፡ በመጨረሻም ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ሲያውጅ ልጆቻቸውን ለነጻነታችሁ ታገሉ ብለው ልከዋል፡፡
የ58 ዓመቱ ጎልማሳ ደጀን አለነ የአባ አለነ አበራ የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ ከወያኔ ጋር በነበረው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከስድስት ቦታ ላይ ተመትቶ ጎንደር ለህክምና ሄደ፡፡ ከወገብ በላይ እና ከወገብ በታች በርካታ ቦታዎች ላይ የተመታው ደጀን ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ሕክምና ተደርጎለት ተመልሷል፡፡ ዛሬ በሰው ተደገፎ የሚንቀሳቀሰው ደጀን የስምንት ልጆች አባት ነው፡፡ ስምንት ልጆች እያሉህ ነበር ውጊያ ውስጥ የገባኽው ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ “እኔ ሞቼ ልጆቼ በነጻነት መኖር ነበረባቸው” ነበር ያለን፡፡
እንቅስቃሴው ሁሉ በሰው እጅ ላይ ያለው ደጀን በጦርነቱ ስላጋጠመው ነገር ሲያወራን ፈገግታው ጉዳት የደረሰበት አይመስልም፡፡ “የተዋጋሁት ለሀገሬ አልነበረም፤ ለእኔ እና ለልጆቼ ነጻነት እንጂ” የሚለው ደጀን አለነ አማርኛ አትናገሩ፣ አትፎክሩ፣ አትዝፈኑ፣ አታልቅሱ ያልተባልነውም፤ ያልኾነውም አልነበረም ይላል፡፡ “ዋይ በሉ ተባልን ያላባታችን ዋይ አንልም አልን” በቃ ጠባቸው ሁሉ አማራ እና አማርኛ ነበር ይላል፡፡ ለልጆቼ ነጻነት ስል የከፈልኩት መስዋዕትነት በመኾኑ ለአፍታም አልከፋም ይላል፡፡
“ወያኔዎች ወልቃይት እንደ ፍየል ቅልጥም ጥማቸዋለችና ነገም አያርፉም” የሚለው ደጀን ከዚህ በኋላ አማራ ነባር እርስቱን ዳግም አሳልፎ ለበይ ላለመስጠት መክፈል ካለበት ሁሉንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርበታል ይላል፡፡ እንዲህ ኾኘ እንኳን ወያኔ የወልቃይትን ምድር ድጋሚ ከሚረግጣት መሞትን እመርጣለሁ ነበር ያለን፡፡ መደራጀት እና መደማመጥ ወቅቱ የሚጠይቀው ትንሹ መስዋዕትነት መኾኑን በመጥቀስ፡፡
ወያኔዎች “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” ይላሉ የሚለው ደጀን አለነ ብዙ ልዩነት ቢኖር እንኳን አሁን የጋራ አጀንዳችን መኾን ያለበት ማንነትን ማስከበር ነው ይላል፡፡ እነርሱ ውሸት ይዘው ለመንፈራገጥ ይሞክራሉ፤ እኛ በአንጻሩ እውነት ይዘን ዝም ብለናል፡፡ ዘመኑ እንደሚጠይቀው መኾን ግድ ይላል ነው ያለው፡፡
በመጨረሻም የወልቃይት ወረዳ አሥተዳደር ደጀን ለከፈለው የጀግንነት ተጋድሎ እና መስዋዕትነት አበርክቶውን የሚመጥን ድጋፍ እና እውቅና እንደሰጡት ነግሮናል፡፡ በሌለ በጀት ወረዳው እና ዞኑ ያደረጉልኝ ድጋፍ እኔን ሳይቀር ቤተሰቤን አስደስቷል፡፡ እንዲህ ያለው ተጎጅዎችን ማስታወስ ሌሎች ጀግኖችን ለማፍራት ያግዛል ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!