
አዲስ አበባ: ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 176 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የ2015 አፈጻጸም እና የ2016 ዕቅድ ላይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ እና ከፍተኛ ግብር ከፋዮቹ በተገኙበት ውይይት እየተደረገ ነው።
በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 183 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የዕቅዱን 96 በመቶ ማለትም 176 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ማሳካቱን የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ኢንሲሱ ገልጸዋል ።
ሥራ አስኪያጁ ባቀረቡት ሪፖርት ካሉት 642 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች 100ዎቹ በኦንላይን እንዲያሳውቁ ታስቦ 96 በመቶዎቹ አሳውቀዋል ብለዋል።
በኢ – ክፍያ የከፈሉት ደግሞ 560ዎቹ (87 ነጥብ 2 በመቶ) መኾናቸው ተገልጿል። በ2015 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በቴሌብር ክፍያ ተፈጽሟል ተብሏል።
በ12 ወራት ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሳወቅ ካለባቸው 7 ሺህ 584 ድርጅቶች ውስጥ 7 ሺህ 554ቱ (99 ነጥብ 6 በመቶዎቹ) በጊዜ አሳውቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ 4 ሺህ 284 (56 ነጥብ 7 በመቶ) ከክፍያ ጋር ያሳወቁ ናቸው፡፡ በበጀት ዓመቱ የንግድ ትርፍ ማሳወቅ ካለባቸው 632 ድርጅቶች ውስጥ 625 አሳውቀዋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በኤክሳይዝ ታክስ በኩል ደግሞ ከ28 ድርጅቶች 2 ብቻ ማሳወቃቸውን አብራርተዋል።
ከተጨማሪ እሴት ታክስ ፣ ከንግድ ትርፍ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ ፣ዊዝሆልዲንግ እና አክሲዮን ትርፍ ድርሻ ባዶ ተመላሽ ኪሳራን በማጣራት 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል አቶ ተሬሳ። ውዝፍ እዳ በተመለከተ 20 ቢሊዮን ታቅዶ 32 ቢሊዮን መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጁ እንዳስታወቁት በ2016 በጀት ዓመት ከ742 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች 226 ቢሊዮን ብር በቅርንጫፍ ለመሰብሰብ ታቅዷል። ይህም እንደሚኒስቴር ከታሰበው 529 ቢሊዮን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
ገቢ ሰብሳቢ ቅርንጫፉ የሰነድ ማቅረቢያ ጊዜን ከወትሮው ወደ 10 ቀን ማራዘሙንና ሌሎች በደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት ሥራዎችን የጀመረ ሲኾን የዛሬው ውይይትም የዚሁ አካል መኾኑን አቶ ተሬሳ ተናግረዋል ።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!