
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 17/2012ዓ.ም (አብመድ) ከሰሞኑ በሞጣ ከተማ በመስጂዶች እና በንግድ ተቋማት ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ለማውገዝ በምሥራቅ አማራ የተለያዩ ከተሞች የተደረገው ሠላማዊ ሰልፍ ያለምንም ችግር መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ልማትና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ ለአብመድ እንደተናገሩት ሠላማዊ ሰልፉ የተደረገው በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች ነው፡፡
በሠልፉም በመስጂዶች ላይ የደርሰውን ውድመት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች አውግዘዋል፡፡ ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትንም ሠልፈኞቹ ማውገዛቸውን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር እና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያስቆምም ሰልፈኞቹ እንደጠየቁ ታውቋል፡፡
ኮማንደር መሠረት እንደገለጹት የየአካባቢው የፀጥታ አካላት ሠላማዊ ሰልፉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውንም አስተታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ