
ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የታሪክ፣ የባህልና የዲፕሎማሲ ትስስር በአግባቡ የሚያንፀባርቅ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።
በሩሲያዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከሩሲያ የዲጅታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ማስ ሚዲያ ምክትል ሚኒስትር ቤላ ቼርኬሶቫ ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም አፍሪካውያን የዓለም አቀፍ የሚዲያ አማራጮቻቸውን ለማስፋት እንዲችሉ በሩሲያ የሚገኙት ትልልቅ መገናኛ ብዙሃን የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃሰተኛ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግግር እና ተመሳሳይ ችግሮች እያመጡ ያሉትን ጉዳት ለመቀነስ ሁለቱ ሀገራት ልምድ ለመለዋወጥና ውጤታማ የሆኑ አሰራሮችንም ለመተግበር ተስማምተዋል፡፡የመንግስት አጀንዳዎችን ለሁሉም ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ወሳኝ መሆኑን ምክትል ሚኒስትሯ አንስተዋል።
ለኢትዮጵያ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠናና የትምህርት እድሎችን ሩስያ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላትም አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ እየሰራች ነው ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የተለያዩ አማራጮችን ለማስተዋወቅ ሚዲያው ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የሁለቱ ሃገራት የሚዲያ ሥራ የሀገራቱን ግንኙነት ወደሚመጥን ደረጃ ከፍ ማለት እንዳለበት ተወያይተዋል። የሩሲያ ሚዲያዎች በአዲስ አበባ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም በሩስያ ቢሮ እንዲከፍቱ እገዛ ለማድረግ መስማማታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!