
ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከጂቡቲ ተጓጉዞ አዲስ አበባ የገባው የአፈር ማዳበሪያ በአስቸኳይ ወደ ክልሎች እንዲሰራጭ ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
ከጂቡቲ ተጓጉዘው ሁለት ቀንና ከዛ በላይ ሳይራገፉ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የቆሙ ከ20 በላይ የጭነት መኪኖች የጫኑትን የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ተራግፎ ወደየ ክልሎች እንዲከፋፈል የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ ሣሪስ አከባቢ በሚገኘው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት ከ20 በላይ የጭነት መኪኖች ሁለት ቀንና ከዛ በላይ አዲስ አበባ ገብተው ማዳበሪያ ሣያራግፉ እንደቆሙ ተመልክተዋል፡፡
በመሆኑም በአስቸኳይ የጫኝ አውራጆችን ቁጥር በመጨመር የተጫነውን ማዳበሪያ በማረጋፍ እንዲሁም በመጋዘን ውስጥ የተከማቸውን ማዳበሪያ ለክልሎች በፍጥነት እንዲከፋፈል ዶ/ር ሶፊያ ለግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ትዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!