
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 17/2012ዓ.ም (አብመድ) በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል እንደተወሰነም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጽሕፈት ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት፣ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት ዘገባዎች ጉዳት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
መግለጫውን በጽሕፈት ቤታቸው የሰጡት የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ሚዲያ አስተባባሪ አቶ ኃይለኢየሱስ አዳሙ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ ሐሰተኛ እና የፈጠራ ዘገባዎች በሕዝብ ሠላም፣ መቻቻል እና መከባበር ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ችግሩ በዝምታ መታዬት የለበትም፤ ጉዳዩን በሚመለከት ረቂቅ ሕግም እየተዘጋጀ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹የማኅበረሰብ አንቂዎች ከተንኳሽ ዘገባዎች በመታቀብ ለሕዝብ ሠላም፣ መቻቻል እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሥራት ይኖርባቸዋል›› ያሉት አቶ ኃይለኢየሱስ ከሀገር ውጪ ያሉ አንቂዎችም ከመሠል ችግሮቻቸው እንዲታቀቡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በውጪ ሀገራት የሚገኙ የማኅበረሰብ አንቂዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያሠራጩት የሀሰት እና የፈጠራ ዘገባ በሕግ የሚጠየቁበት አሠራር ይኖራልም ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ሀገራዊ ለውጥ ያልፈለጉ አካላት ሠላም እንዳይኖር አስበውና አቅደው ከሚሠሩባቸው ተቋማት ውስጥ ዋነኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሀገሪቱ ሠላም የለም›› ለማለት ከመስከረም ጀምረው ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ተቋማት እንዳይሄዱና በየክልሎቻቸው እንዲማሩ ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር ያስታወሱት የማኅበራዊ ሚዲያ አስተባባሪው ‹‹ይህ አልሆን ሲላቸው በየተቋማቱ ብጥብጥ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው›› ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የፀጥታ ችግር የመማር ማስተማር ሥራው ተቋርጦ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ተቋማት ችግሩ ቢከሰትም ችግሩን በፍጥነት በመፍታት ወደ ሠላማዊ መማር ማስተማር ሥራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በበርካታዎቹ ዩኒቨርሲቲዎችም ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሥራዎች እየተካሄዱ ነው›› ያሉት አቶ ኃይለኢየሱስ ተከታታይ ሥራዎች በሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ተቋማት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይም ተመሳሳይ የሆነ ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አስተባባሪው ተማሪዎቹ በየተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ እንደተወሰነም ገልፀዋል፡፡ ተቋማቱ በፌዴራል ልዩ ኃይል ጥበቃ እንደሚደረግላቸው እና የደኅንነት ስጋቶች እንዳይኖሩ እየተሠራ መሆኑም ተግልጧል፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ከምሽቱ 1፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ መከልከሉን እና ከምሽት 4፡00 በኋላ ከዶርማቸው ውጪ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑንም አቶ ኃይለኢየሱስ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው