“በአማራ ክልል በአንድ ዓመት ውስጥ 60 ሺህ ሰዎችን የዓይን ቆብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል” ዶክተር መልካሙ አብቴ

41

ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ትራኮማን በመከላከልና መቆጣጠር ሥራው የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ለመገምገምና በቀጣይም በሽታውን ለማስወገድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን ጨምሮ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው። በተለይም የትራኮማ በሽታን በክልሉ ነጻ ለማድረግ ከካርተር ሴንተርና ሌሎችም አጋር አካላት ጋር የሚደረገው ርብርብ አበረታች ነው ብለዋል።

ቢሮ ኀላፊው እንዳሉት በዚህ አንድ ዓመት 60 ሺህ ሰዎችን የዓይን ቆብ ቀዶ ጥገና አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ከዓይን ጤንነት ጋር በተያያዘ 21ሺህ 45 ሰዎች የዓይን ቆብ ቀዶ ጥገና ተሠርቶላቸዋል ነው ያሉት። ከለጋሽ አካላት እስከ ሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋናቸው አቅርበዋል።

ካርተር ሴንተር የትራኮማ በሽታን ከአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በሚያስችል ኹኔታ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ነው ያሉት ደግሞ በካርተር ሴንተር የአማራ ክልል ኀላፊ ፈጠነ ምሕረቱ ናቸው።

ኀላፊው እንዳሉት በክልሉ 62 ወረዳዎችን ከትራኮማ ነጻ በማድረግ ከመድኃኒት እደላ ውጭ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ኀላፊው በሽታው ከክልሉ እስኪጠፋ ድረስም ካርተር ሴንተር ከክልሉ መንግሥት ጋር በጋራ ይሠራል ብለዋል።

ኃላፊው አሁንም በክልሉ ከ70 እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የትራኮማ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተናገሩት።

በመድረኩ የተገኙት የካርተር ሴንተር የትራኮማ መቆጣጠር ፕሮግራም ዳይሬክተር ኬሊ ካልንኽን በአማራ ክልል ትራኮማን የመከላከል ሥራው ስኬታማ ነው ብለውታል። በተለይም ከአጋር አካላት ጋር የተደረገው ቅንጅታዊ አሥራር በየትኛውም ዓለም እና በሀገሪቱም በየትኛውም ክልል ያልታየ የመከላከልና የመቆጣጠር፣ የሕክምና አገልግሎት ነው ብለዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማእረግ የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን በመድረኩ እንደተናገሩት ትራኮማን ለመከላከል የሚያስችል ውሳኔ ላይ መድረስ ከቻልን በቀላሉ የምንከላከለው ነው ፣በችግር ላይ ተኹኖም የታዩት ጅምሮች ለስኬት የሚያበቁ ናቸው ብለዋል።

አቶ ስዩም የትራኮማ በሽታን ለመከላከልና ለማስወገድ ለንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽነት ቆርጠን መነሳትና የማኅበረሰብን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ሁሉም በኃላፊነቱ ልክ እንዲሠራ አሳስበዋል።

ልንከላከለው በምንችለው ቀላል በሽታ ኅብረተሰቡ ለዓይነ ሥውርነትና በኢኮኖሚም ለመዳከም እንዲበቃ ኾኗል፣ይህ የክልሉን ሕዝብ የማይመጥን ነው ብለዋል። የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፣ በቅርብ ዓመታትም ከትራኮማ በሽታ ነጻ የኾነ ክልል መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዓለም የሥራ ድርጅት የሠራተኞችን አቅም በመገንባት ተወዳዳሪ ሠራተኞችን እየፈጠረልን ነው።” አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ
Next articleአዲስ አበባ የገባው የአፈር ማዳበሪያ በአስቸኳይ ወደ ክልሎች እንዲሰራጭ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።