
ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የሥራ ድርጅት ከአማራ ክልል ሥራ እና ስልጠና ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የዓለም የሥራ ድርጅት የፕሮአግሮ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አንቶኒዮ ኤጀንታ፣ የዓለም የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ጁሊየስ፣ የአማራ ክልል ሥራ እና ስልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደን ጨምሮ የልዩ ልዩ ቢሮ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው አደንግዶች እየተሳተፉ ነው።
የዓለም የሥራ ድርጅት የፕሮአግሮ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አንቶኒዮ ኤጀንታ ፕሮጀክቱ በዋናነት ሁለት ነገሮችን ማለትም ሥልጠና መሥጠት፣ እና ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የሚሠሩበትን መንገድ ማመቻቸት ከሚሠራቸው ሥራዎች ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል። እስካሁን ብዙ ሠርተናል አሁንም አዲስ ፕሮጀክት ይዘን መጥተናል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደ የዓለም የሥራ ድርጅት ባለፉት ሦስት ዓመታት በሥራ እድል ፈጠራ እና በስልጠና ዙሪያ ከክልሉ ጋር እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይ ሥራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ የሥራ የመረጃ ሥርዓትን በመዘርጋት ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ እንዲቀጠሩ ያደርጋል። ከተቀጠሩ በኃላም ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲፈጠር እና ለሥራ ፈላጊዎች ሥልጠና ይሠጣል ብለዋል። የግብርናውን እና የኢንቨስትመንት ዘርፉን በመደገፍ ወጣቶች በዘርፉ እንዲሠማሩ እና ውጤት እንዲያስመዘግቡ እያደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ቢሮ ኀላፊው የአለም የሠራ ድርጅት በደሮ እርባታ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት፣ እንስሳት በማድለብ የተሠማሩ ወጣቶች እስከመጨረሻው እንዲዘልቁ እና ውጤት እንዲያስመዘግቡ እያደረገ ነው ብለዋል።
የዓለም የሥራ ድርጅት በግብርና ምርት ላይ የእሴት ሰንሰለቱን በመጠቀም አዲስ የሥራ እድል ለመፍጠር ፕሮጀክት ይዞ መምጣቱ ለወጣቶች ጥሩ አጋጣሚ መኾኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ በበጀትም በቴክኒክም ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ክልሉ ከዚህ ቀደም የነበረውን ግንኙነት በማጠናከር አዲሱን ፕሮጀክት ውጤታማ ለማድረግ እንሠራለን ነው ያሉት።
በዓለም የሥራ ድርጅት የፕሮአግሮ ፕሮጀክት የሥራ ሥምሪት እና የእስኪል ዲቨሎፕመንት አስተባባሪ አያሉ አድማስ ደርጅቱ መንግሥትን፣ አሠሪ ድርጅቶችን እና የሠራተኛ ማኅበርን በማቀናጀት የሚሠራ ድርጅት ሲሆን ፕሮጀክቱ በሲዳማ እና በአማራ ክልል ይሠራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመት የሚቆይ ሲኾን የውጭ ኢንቨስተሮች ወደሀገር ውስጥ ገብተው ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩ እያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል። ግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ሥልጠናዎችን መሥጠት፣ አካባቢን ለሥራ ምቹ ማድረግ፣ የዓለም የሥራ ህግጋቶችን እንዲገነዘቡ ማድረግ ዋና ዓላማቸው መኾኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በጀርመን መንግሥት ድጋፍ የሚሠራ ሲኾን የፖሊሲ ድጋፍ እና ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ እና ውጤት ማምጣት ላይ እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ተወካይ ዳይሬክተር ሙጨ ሽፈራው ድርጅቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደሀገር እንዲመጡ የሥልጠና ሥርዓት በመዘርጋት እየሠራ ነው በዚህም የተለያዩ ኢንቨስተሮች ወደ ኢንዱስትሪፓርክ እየገቡ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!