
መንግሥት ተማሪዎች ወደ መሠናዶና በሂደትም ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ለምደባ ይሠራበት የነበረውን ለተፈጥሮ ሳይንስ 70 በመቶ እንዲሁም ለማኅበራዊ ሳይንስ 30 በመቶ የምደባ ሥርዓት ለተፈጥሮ ሳይንስ 55 በመቶ እንዲሁም ለማኅበራዊ ሳይንስ 45 በመቶ እንዲሆን መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬከተር ደቻሳ ጉርሙ ለኢትዮጵያ ሄራልድ እንደገለጹት ብሎ ኢ.ፕ.ድ እንደዘገበው ከዘንድሮው የትምህርት ዘመን ጀምሮ መንግሥት ለዓመታት ሲሠራበት የቆየውን የተፈጥሮ ሳይንስና ማኅበራዊ ሳይንስ የተማሪዎች ድልድል ከ70፡30 ወደ 55፡45 ቀይሯል።
መንግሥት ቀደም ሲል ለዓመታት ሲሠራበት የቆየው የ70፡30 የድልድል ሥርዓት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የታሰበውን የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ፤ በርካታ ተማሪዎች ያለፍላጎታቸው የተፈጥሮ ሳይንስን እንዲመርጡ የሚያስገድድና በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ውጤታማ መሆን አለመቻላቸው፤ የዩኒቨርስቲዎች የመቀበል አቅምን በማገናዘብና የሀገሪቱን የሰው ሀብት ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባትና በመሳሰሉት ምክንያቶች የምደባ ሥርዓቱን መቀየር አስፈልጓል።
በዘንድሮ ትምህርት ዘመንም በሀገሪቱ በሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች 142 ሺህ 900 ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፤ አዲስ በተዘረጋው የምደባ ሥርዓትም ሁሉም ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ መርጠው ለመማር ምቹ ዕድል እንደሚፈጠር አቶ ደቻሳ ተናግረዋል።
አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ይልቅ ከማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተመርቀው ለሚወጡ ዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት እንዳሉም ዳይሬክተሩ ገልጸው ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባትም 200 የሚደርሱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተፈጥሮ ሳይንስ ይልቅ ማኅበራዊ ሳይንስን መርጠው በማስተማር ላይ ይገኛሉ።
ድልድሉ ከ70፡30 ወደ 55፡45 መቀየሩም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የሥራ ዕድሎችን አሟጥጦ ለመጠቀምና ዜጎችም በፍላጎታቸው በተማሩበት መስክም ሥራ ለመያዝ የሚያስችላቸው እንደሚሆንም አቶ ደቻሳ አስረድተዋል።