“በዞኑ ከ4 መቶ 30 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመኸር ለማልማት እየሠራን ነው” የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ

35

ደሴ: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የመኸር እርሻ ሥራ በጃማ ወረዳ አስጀምሯል።

መሬታቸውን በማለስለስ የተሻለ ምርት እንዲሰጥ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት በጃማ ወረዳ የ08 ቀበሌ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም በመዝራታቸን ተጠቃሚ እንኾናለን ብለዋል።

የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ እጥረት አለ ያሉት አርሶ አደሮቹ ችግሩ እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል። የጃማ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መርእድ አድማሱ በወረዳው 40 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር እርሻ እንደሚሸፈን እና ከዚህም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
በዞኑ 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በእቅድ ተይዟል ያሉት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በዞኑ ስድስት የተለያዩ ሰብሎች በኩታ ገጠም ለማልማት በተለያዩ ወረዳዎች እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ 4 መቶ 30 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ ገልጸው እስካሁንም ከ250 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች የሚያነሱት የማዳበሪያ እጥረት ጥያቄ ትክክል ነው ያሉት ኀላፊው ዞኑ 519 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ የሚያስፈልገው ቢሆንም እስካሁን ግን 260 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ብቻ ማሰራጨት እንደተቻለ ነው የጠቆሙት።

በቀጣይ ወደ ዞኑ የሚመጣውን ማዳበሪያ ከሕገ-ወጥ ደላሎች ነፃ በማድረግ በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሩ ለማከፋፈል እንደሚሠራ መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።

ዘጋቢ:-ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮ ቴሌኮም ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል ገመድ አልባ የኔትወርክ ዝርጋታ እንደሚያካሂድ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናገሩ።
Next article“የዓለም የሥራ ድርጅት የሠራተኞችን አቅም በመገንባት ተወዳዳሪ ሠራተኞችን እየፈጠረልን ነው።” አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ