የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲቲዩት፤ ግብርና ሚኒስቴር እና የፈረንሳይ ልማት ተራድኦ ድርጅት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ አደረጉ፡፡

53

አዲስ አበባ: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲቲዩት፤ ግብርና ሚኒስቴር እና የፈረንሳይ ልማት ተራድኦ ድርጅት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ለግብርና ሥራ ማስኬጃ የሚኾን 32 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድርገዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ.ር) ድጋፉ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለተጎዱ ለአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልል እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

✍️ ድጋፉ በሦስቱ ክልሎች የሚገኙ 50 ወረዳዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ረሚ ማሬቻውስ ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም እና ወደ አምራችነት ለመመለስ ታስቦ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
✍️ድጋፉ በሦስቱም ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እኩል ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

የአውሮፖ ኅብረት ተወካይ ዴቪድ ክሪቫኔክ ድጋፉ ወቅቱን የጠበቀ እና አስፈላጊ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

✍️ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ተዳክሞ የነበረውን አምራች ማኅበረሰብ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) የአማራ ክልል አምራች ማኅበረሰብ በነበረው ጦርነት ምክንያት ላለፉት ሦስት ዓመታት ተጎድቶ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
✍️በዚህም ግብርናው ተቀዛቅዞ እንደነበርና በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት ከ92 ቢሊዮን ብር በላይ በግብርናው ዘርፍ ጉዳት እንደደረሰ አብራርተዋል፡፡

✍️ ለአማራ ክልል አሁን የተደረገው የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ በክልሉ ከሚገኙ 9 ዞኖች መካከል 6 ዞኖችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡

✍️በክልሉ አምራቹን ማኅበረሰብ አሁንም ወደነበረበት ለመመለስ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶክተር ኃይለማርያም አሁን የተደረው ድጋፍ ችግሩን እንደሚያቃልለው እና አስፈላጊ እንደኾነ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ በረዶና ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በቤትና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ።
Next articleኢትዮ ቴሌኮም ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል ገመድ አልባ የኔትወርክ ዝርጋታ እንደሚያካሂድ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናገሩ።