የሕፃናት ማቆያ በማዘጋጀት የሴት ሠራተኞቹን ችግር መፍታት መቻሉን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

83

ደብረ ታቦር: ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕፃናት ማቆያ በማዘጋጀት የነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙና እናቶችም ተረጋግተው እንዲሠሩ ማድረጉን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል፡፡

ጫቅላ ሕፃናት ያላቸው የመምሪያው ሰራተኞች ለልጆቻቸው ማቆያ ስለተዘጋጀላቸው ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ጸጋየ እና ወይዘሮ እንዳሉ እንዳየሁ የመምሪያው ሠራተኛ ሲኾኑ የሚያጠቡት ሕፃን ልጅ አላቸው፡፡ ሠራተኞቹ ሕፃን ልጆቻቸውን ከቤት ትተው መስሪያ ቤት ገብተው በሙሉ ልባቸው ሥራቸውን ለመከወን ይቸገሩ እንደነበርም ነው ያስረዱት፡፡

በዚህም ምክንያት ለልጆቻቸው ተገቢ እንክብካቤ ሲያደርጉ አለመቆየታቸውን ነው ለአሚኮ ያብራሩት፡፡

አሁን ላይ እናቶቹ መሥሪያ ቤታቸው የሕፃናት ማቆያ በማዘጋጀቱ መደሰታቸውን ገልጸው አመሥግነዋል፡፡ በቀጣይም እንደ ሕፃናቱ የዕድሜ ደረጃ የሚመጥን ቁሳቁስ እንዲዘጋጅላቸው ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲስ ተፈራ በመሥሪያ ቤታቸው የሴት ሰራተኞችን ችግር በመረዳትና ለሕፃናት የወደፊት እድገት ትኩረት በመሥጠት ማቆያው እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡ወደፊትም አስፈላጊው ነገር ሁሉ እየታየ እንደሚሟላ ነው የተናገሩት፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ የሕፃናት መብት ደኅንነት ቡድን መሪ መላሽ ክንዴ ግብርና መምሪያው ለጀመረው አርዓያነት ያለው ተግባር አመሥግነዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በሐምሌ 2010 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ ሴት የመንግሥት ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታቸው ሕፃናት ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ቦታ እንዲዘጋጅላቸው መመሪያ ስለማውጣቱም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ በዞኑ መመሪያው እየተተገበረ አለመኾኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ተቋማት የሕፃናት ማቆያ እንዲያዘጋጁ መምሪያው የግንዛቤ ፈጠራ እየሠራ መኾኑን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በማንነታችን ላይ ዳግም ለአፍታ እንኳን ተዘናግተን የተራዘመ መከራ እና ባርነት ለመቀበል ፍጹም አንፈቅድም” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ በረዶና ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በቤትና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ።