‹‹የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ አጭርና ግልፅ ነው፤ በሀገሩ ነፃነትን፣ ፍትሕን እና እኩልነትን ማስፈንና በጋራ መኖር ነው፡፡›› ብልፅግና ፓርቲ

405

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 17/2012ዓ.ም (አብመድ) የብልጽግና ፓርቲ አማራ ክልል ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘመናት መካከል የመሪነት ዕድል አግኝተው ወደ ስልጣን የወጡ መንግሥታት እና የአስተዳደር ሥርዓቶች አልመች ባሉ ጊዜና ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ባጋጠሙ ጊዜ ለፍትሕ፣ ለነፃነት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሌሎች ክልል ሕዝቦች ጋር በጋራ የአማራ ሕዝብ ታግሏል፡፡

‹‹ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ሕዝቦች ጋር በመቻቻል እና በሠላም ለመኖር ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያመላክቱት በክልሉ ውስጥ የሚገኙት ስብጥር ማንነቶች እና ልዩ ልዩ እምነቶች ማሳያዎች ናቸው›› ያሉት የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ አስተባባሪ ኃይለኢየሱስ አዳሙ ናቸው፡፡ ‹‹በዚህ የመቻቻል እና የመከባበር እሴት ውስጥ ሆኖ የአማራ ሕዝብ ፍላጎቱን በሌሎች ላይ ለመጫን እና የሌሎች ፍላጎት እንዲጫንበትም የማይፈልግ ሕዝብ ነው›› ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄም በሀገሩ ነፃነትን፣ ፍትሕን እና እኩልነትን ማስፈንና በጋራ መኖር ነው›› ብለዋል አቶ ኃይለኢየሱስ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራ ሕዝብ የመቻቻል እሴት መገለጫ የሆኑት የሃይማኖቶች መከባበር እና አብሮነት እንዲጠለሽ እና ሌላ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡ በክልሉ ውስጥ በክፉና ደጉ በጋራ ዘመንን መሻገር በለመዱት የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች መካከል ግጭት በመፍጠር ክልሉን ወደ ከፋ ብጥብጥ ለማስገባት በተደጋጋሚ ቢሞከርም በሠላም ወዳዱ ሕዝብ መክሸፉን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር በተፈጠረው ግጭት ‹‹85 ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል›› ያሉት አቶ ኃይለኢየሱስ 46 በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው በ31 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የመመሥረት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቀሪዎቹ 15 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ጣቢያ ማረፊያ ቦታዎች ላይ ቃል እየሰጡ እና ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በሕግ ቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይለኢየሱስ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሕዝቡ አጋዥ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸውን መስጂዶች መልሶ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የባንክ ሒሳብ መከፈቱንም አስታውሰዋል፡፡ ወጣቶች ምክንያታዊ በመሆንን ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ መመርመር እንደሚኖርባውም አሳስበዋል፡፡ አቶ ኃይለኢየሱስ ሞጣ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚናፈሰው ሳይሆን ሠላማዊ እንቅስቀሴ ውስጥ እንደሆነችም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleበክልሉ የተደረጉ ሠላማዊ ሰልፎች በሠላም መጠናቀቃቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
Next articleየብልፅግና ፓርቲ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የፈጠራ ዘገባዎች በሕዝብ ሠላም ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሆኑ ገለጸ፡፡