የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሱዳን ተሰደው በመተማ ወረዳ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ አደረገ።

49

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በሱዳን በተፈጠረው ጦርነት ከሱዳን ተሰድደው በመተማ ወረዳ ተጠልለው ለሚገኙ 4ሺህ ስደተኞች ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን ያስረከቡት በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማኅበር የሰሜን ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አታለል ታረቀኝ ለሥደተኞች የተደረገው ድጋፍ የቁሳቁስ መኾኑን ተናግረዋል።

✍️ የተደረገው ድጋፍ ከተፈናቃዩ ብዛት አኳያ በቂ አለመኾኑን የገለጹት አቶ አታለል ማኅበሩ እያደረገ ያለውን ሰባዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

✍️ ማኅበሩ ድጋፉን የሚያሰባስበው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው ያሉት ኀላፊው ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ኢትዮጵያውያን ማኅበሩን በመደገፍ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ አቶ አታለል ገለጻ የኢትዮጵያ ቀይ መሥቀል ማኅበር ከዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለሥደተኞች እስካሁን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልኾነ ድጋፍ አድርጓል።

ተፈናቃዮች ክረምቱን ተከትሎ አስቸጋሪ ኹነት ውስጥ መኾናቸውን አንስተው የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው ገልጸዋል።

✍️ ለተደረገላቸው ድጋፍም አመሥግነው በቀጣይ መንግሥትና ሌሎች ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በሱዳን በሁለቱ ተፋላሚ ኀይሎች በተፈጠረው ጦርነት አሁን ላይ ሱዳናውያንን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ በኾነችው መተማ ዮሐንስ እየገቡ ይገኛሉ።

ጦርነቱ ከተጀመረ እስካሁን ከ71ሺህ በላይ የሚኾኑ የ74 ሀገራት ዜጎች ሸሽተው ወደ መተማ ዮሐንስ ከተማ ገብተዋል። ከእነዚህ መካከልም ከ34ሺህ በላይ የሚኾኑት ኢትዮጵያውያን መኾናቸውን ከምዕራብ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮምኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ቀብታ ሁመራ፣ የበጌ ምድር ግዛት እንጂ የትግራይ አካል ኾነው አያውቁም” አቶ ገ/መድህን አርአያ፣ የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የሥራ አመራር የነበሩ
Next articleየኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በግብጽ አዲስ እየተገነባ ያለውን የካይሮ ከተማ ጎበኙ።