
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 17/2012ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በተመረጡ ሦስት ወረዳዎች ድርቅና የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ይፋ ተደርጓል፡፡
የዓለም ባንክ በ2018 (እ.አ.አ) ባወጣው መረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 109 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥርም በሕዝብ ብዛቷ ከናይጄሪያ በመቀጠል ሁለተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ያደርጋታል፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እንደሆነም መረጃው ጠቁሟል፡፡
ዓመታዊ ምጣኔዋም በአማካይ 9 ነጥብ 9 በመቶ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በ2025 ደግሞ መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ እየሠራች መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ዓመታዊ የነብስ ወከፍ ገቢው 790 የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ መረጃው ኢትዮጵያ እያደገች ያለች ሀገር እንደሆነች ቢገልጽም የዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ኢትዮጵያንና መሠል ሀገራትን የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የዓለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል የድርቅ አደጋ ምላሽ ሰጪ ፕሮጀክት (GCF) አንዱ ነው፡፡ ይህ ድርጅት በኢኮኖሚ ላቅ ያሉ 33 የዓለም ሀገራት የመሠረቱት ድርጅት ነው፡፡ ያደጉት ሀገራት በሚለቅቁት በካይ ጋዝ የአየር ንብረት ላይ ተፅዕኖ የሚደርስባቸውን ሀገራትን ለመካስ ድጋፍ የሚያርግ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ለኢትዮጵያ በቀጣይ አምስት ዓመታት በውኃ አቅርቦትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሚተገበር 45 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ከ45 ሚሊዮን ዶላሩ 154 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በአማራ ክልል ይተገበራል ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ባለሙያ አስናቀው የኋላ እንደተናሩት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር ከአምስት ዓመታት በፊት በጋራ የቀረጹት ፕሮጀክት ነበር፡፡
በአማራ ክልል በተመረጡ ሦስት ወረዳዎች እንደሚተገበርም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸውን ወረዳዎች ፕሮጀክቱን የቀረጹት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዳጠኑት የገለጹት ባለሙያው ታች ጋይንት፣ እነብሴ ሳር ምድር እና ላስታ ወረዳዎች ላይ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡
የውኃ አቅርቦቱ በፀሐይ ብርሃን እንደሚሠራ፣ ንጹህ መጠጥ ውኃ ለመጠቀምና ለመስኖ አገልግሎት እንደሚውል ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱ በተለይም ሴቶች የልማት ተደራሸነታቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡ በተመረጡት ወረዳዎች በእያንዳንዳቸው ሦስት ለድርቅና አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መመረጣቸውንም አቶ አስናቀ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ