
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን የመዋቅር ለውጥ አካሂዷል። አዲሱን መዋቅር የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አስተዋውቋል።
“አሚኮ ወደ አዲስ ምዕራፍ” በሚል የተዋወቀው አዲሱ መዋቅር ላለፉት ጊዜያት ከአማራ ምሁራን መማክርት ጋር በጋራ ሢሠራ ነው የቆዬው።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ባስተላለፉት መልእክት ተቋሙ ጊዜውን በሚዋጅ መልኩ ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዋጅ መቀየሩን አስታውሰዋል። ተቋሙ የመለያ ቀለሙንም አሻሽሏል፣ ሁለተኛ የቴሌቪዥን ቻናል ከፍቷል፣ ደሴ ላይ ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም እየገነባ ነው፣ አዲስ አበባ ላይ አስተዋፅኦውን ማሳደግ የሚያስችለው ቦታ ተቀብሏል ነው ያሉት።
አሚኮ የውስጥ ገቢውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መኾኑንም ተናግረዋል። በነበረው የወረራ ጦርነት ወልድያና ደሴ ላይ የሚገኙ ቅርንጫፎቹ ሙሉ ለሙሉ ወድመው እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስፈፃሚው የደሴን ስቱዲዮ ባለ አቅም ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ነው የተናገሩት።
አሚኮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ መኾኑንም ገልጸዋል።
ተቋሙን የሚደግፉ የክልል መሪዎች፣ የሥራ አመራር የቦርድ አባላት እንዳሉትም ገልጸዋል። አሚኮ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ዋናው ዓላማው ለሕዝብ የሚሠራ፣ ጠንካራና መፍትሔ አመላካች የሚዲያ ተቋም ለመገንባት መኾኑን አንስተዋል።
በአንድነት ከሠራን የጠንካራ ተቋም መሠረት እንጥላለን፣ በቀጣይም ጠንካራ ተቋም ለትውልድ እናስተላልፋለን ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የራሱን አሻራ ያሳረፈ፣ የራሱ ቀለም ያለው፣ ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚተጋ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል።
ተቋሙ የተከማቸ ትልቅ ተቋማዊ እሴት እንዳለውም ተናግረዋል። ተቋሙ ለሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች መትጋት እንደሚገባውም ተናግረዋል። የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጋራ ኾኖ ማለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሚኮ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የክልሉ መንግሥት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ለአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ አባላትና ለአማራ ምሁራን መማክርት ላደረጉት አስታውጽዖም ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!