
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን የመዋቅር ለውጥ አካሂዷል።
አዲሱን መዋቅር የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አስተዋውቋል።
የክልሉን መንግሥት ወክለው መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አሚኮ ከትንሽ ነገር ጀምሮ ታላቅ ተቋም መኾን የቻለ መኾኑን ገልጸዋል።
ያለንበት ዓለም ተለዋዋጭ በመኾኑ የሚዲያ ተቋማትም ጊዜውን የሚመጥን ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተናገሩት።
የክልሉ መንግሥት አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለክልሉ አስፈላጊ መኾኑም በማመን በትኩረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፉን እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ሚዲያው እንዲያድግ የሥራ አመራር ቦርዱ በትኩረት መሥራቱንም አስታውሰዋል። አሚኮ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲኾን ሥራዎች ሲሠሩ መቆዬታቸውን ነው የገለጹት።
አሚኮ የክልሉን ሕዝብ አንድነት የማጠናከር፣ የክልሉን ሕዝብ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ በትክክለኛው ማንነቱ እንዲታወቅ የማድረግ ሥራ የመሥራት ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት።
ችግሮችን ያገናዘበ እና ችግሮችን በትጋት የመወጣት ኃላፊነት እንዳለበትም ነው የገለጹት። የተቋሙ አዲስ መዋቅር በተገቢው እንዲተገበር የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!