
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን መዋቅራዊ ለውጥ አካሂዷል።
አዲሱን መዋቅር የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አስተዋውቋል።
በአሚኮ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሽግግር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ አሚኮ ይዞት የሚንቀሳቀሰው ዓላማ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል። አሚኮ እየሠራው ለመጣው ታላቅ አስተዋጽዖ ምስክር መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አልፎም ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ መሆኗን ያነሱት አፈጉባዔዋ አሚኮ እንደ ሚዲያ ሕብረ ብሔራዊነቷ የተጠበቀ ሀገር የመገንባት አደራ አለበት ነው ያሉት።
ሕብረ ብሔራዊት ሀገርን የመገንባት ሂደቱ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት የተናገሩት አፈጉባኤዋ በዚህ ሂደት አሚኮ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ከራስ በላይ ማሰብና ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
ወጥቶ ወርዶ የሕዝብን ችግር የሚፈታ፤ ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ሃሳብ የማመንጨት ኃላፊነትን መውሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አሚኮ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት አደራ የጣሉበት ተቋም መሆኑንም አንስተዋል። በመኾኑም አደራ የምንወጣ፣ የበኩላችን ድርሻ የምናበረክት፣ አንድነትን የምናጠናክር መሆን አለብንም ብለዋል።
ጠንክሮ በመሥራት ክልሉን፣ ተቋሙን እና ሀገርን ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባልም ብለዋል። አሚኮ ከሀገር አቀፍ ደረጃም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን እንደሚሠራና ከጎኑ መኾኑን አረጋግጠዋል።
የክልሉ ሕዝብ የነበረውን ሞራልና ልእልና ከፍ ማድረግ እና ልዕልናውን የመጠበቅ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከባዶ አንነሳም ያሉት አፈጉባኤዋ አባቶች የገነቡትን የሞራል ልዕልና በሚያስከብር መልኩ በታማኝነት እና በእውነት ላይ በመመሥረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!