“አሚኮ የክልሉ ውበትና የሕዝቡ ሥነ ልቦና የሚገለፅበት ነው” ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር)

38

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን የመዋቅር ለውጥ አካሂዷል። አዲሱን መዋቅር የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አስተዋውቋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር) ባስተላለፉት መልእክት ሚዲያ ሰላምንም፣ ፀብንም ሊያመጣ ይችላል፣ ሚዲያ ልማትንም ጥፋትንም ሊያመጣ ይችላል፤ በመሆኑም ሚዲያን በሚገባ መጠቀምና ለተፈለገው በጎ ዓላማ ማዋል ይገባል ነው ያሉት።

አሚኮ የአማራ ክልል የሰላም፣ የልማት መስተዋውት ነው፤ የክልሉ ውበትና የሕዝቡ ሥነ ልቦና የሚገለፅበት ነውም ብለዋል። ክልሉ ያለበትን ሁኔታ አሚኮ ላይ ማዬት እንደሚቻል እና የክልሉ መሥታወት መሆኑን ነው ያነሱት።

ክልሉ የማያቋርጥ ፈተና ውስጥ መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር ዓለማየሁ የተረጋጋ የሰላም አጀንዳ እንዲኖር፣ የልማት እንቅስቃሴ እንዲፈጠር፣ ያሉ ችግሮችን በተጨባጭ መውጣትና መፍትሔውን ማሳየት ይገባል ነው ያሉት። የክልሉን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሥፍራዎች ማስታዋወቅ፣ ኪነጥበባዊ በሆነ መንገድ እያዝናኑ ማስተማር ይጠበቅበታል ብለዋል።

አሚኮን የሚመጥን ሥራ ለመሥራት ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እና ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል። ተቋሙ የሚጠበቅበትን ሥራ እንዲሠራ የለውጥ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል። አዲሱ መዋቅር የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተሞክሮ እንደተወሰደበትም ገልፀዋል።

ለውጥ ለማምጣት የኔ ብሎ የሚሠራ የተቋም ሠራተኛ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ሀገሩን የሚወድ ሰው በሚሠራበት ተቋም ትክክለኛ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሚዛናዊነት እና ሐቅኝነት ላይ በመመሥረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። የቡድን ሥራን በአግባቡ መጠቅም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን እና ልማትን አስከብሮ በመቀጠል በልማቱ ዘላቂ ተጠቃሚ መኾን እንደሚገባ ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ተናገሩ፡፡
Next article“አሚኮ ኅብረ ብሔራዊነቷ የተጠበቀች ሀገር የመገንባት አደራ አለበት” የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ