
ጎንደር: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአትክልት እና ፍራፍሬ ተጠቃሚ መኾን መጀመራቸውን የላይ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
አርሶ አደር ብርሃኑ ጸጋ በላይ አርማጭሆ ወረዳ የከቻኒት ውኃ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡
✍️አርሶ አደሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሉት የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነው ለአሚኮ የተናገሩት። ከዚህ በፊት ከነበራቸው የእርሻ ማሳ በመቀነስ በአትክልት እና ፍራፍሬ የሸፈኑት አርሶ አደሩ አሁን ላይ ከውጤቱ ተጠቃሚ መኾን መጀመራቸውን ነው ያስረዱት። አትክልት እና ፍራፍሬው ከራሳቸው አልፎ ወደ ገበያ በማቅረብ በሚያገኙት ገንዘብ ቤታቸውን በአግባቡ መምራት እንዳስቻላቸውም ነግረውናል።
✍️የአርሶ አደር ብርሃኑን ስኬት የተመለከቱ ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን መትከል መጀመራቸውን ገልጸዋል። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በዚህ ዓመት 118 ሚሊዮን የደን ችግኝ እና 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ እንደሚተከል የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አቤ አስፋው ገልጸዋል። ምክትል ኀላፊው አትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ባለፈም የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር በማስተካከልም ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት።
የላይ አርማጭሆ ወረዳ የጌሾ ምርት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አቤ በቀጣይ ሌሎች የፍራፍሬ ምርቶቹን የገበያ ትስስር ለመፍጠር ይሠራል ብለዋል።
✍️የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በበኩላቸው የመጀመሪያ ዙር የችግኝ ተከላ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ዙር መሽጋገሩን አስረድተዋል፡፡
✍️ኀላፊው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ በዚህ ዓመት እንደሚተከልም አስረድተዋል።
✍️ከዚህ ውስጥ ደግሞ 25 በመቶ የሚኾነው የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
✍️የሚተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር ከማስተካከል ባለፈም በምግብ ዋስትና እራስን ለመቻል የሚሠራው ተግባር አንዱ አካል ነው ብለዋል።
✍️የአማራ ክልል ለቡና ምርት አመች በመኾኑ በአማካይ እስከ 14 ኩንታል በሄክታር ማግኘት የሚቻል በመኾኑ ኅብረተሰቡን ከዚህ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የላይ አርማጭኾ ሕዝብ ሰላሙን እና ልማትን አስከብሮ መኖር የቻለ ታታሪ ሕዝብ ስለመኾኑ የሚሠራው ሥራ ማሳያ እንደኾነ ገልጸዋል።
✍️ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰላምን እና ልማትን አስከብሮ የመኖር ተግባርን በቀጣይ አጠናክሮ በመቀጠል በልማቱ ዘላቂ ተጠቃሚ መኾን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ
📷 የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮምኒኬሽን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!