በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ማኅበራት አገልግሎታቸውን የሚያሻሽል አሠራር ዘረጉ፡፡

261

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 17/2012ዓ.ም (አብመድ) በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ማኅበራት ፓርኩን ከጉዳት ለመጠበቅና የቱሪስት አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችል የጋራ አሠራር መዘርጋታቸው ታውቋል፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት ማኅበራቱ ፓርኩን ከጉዳት ለመጠበቅና የቱሪስት አገልግሎቱን ለማዘመን የጋራ አሠራር ዘርግተዋል፡፡ የአስጎብኝ፣ የምግብ አብሳይ፣ የፈረስ ጫኝ፣ የሆቴልና ምግብ ቤት አገልግሎት ሰጭ፣ የዕቃ አከራይ ማኅበራት የጋራ አሠራሩን ከመሠረቱት መካከል ይገኙበታል፡፡

የማኅበራቱ ጥምረታዊ አሠራር በአገልግሎት አሰጣጡ የሚታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል፣ ድክመቶችን ለመቅረፍና የቱሪስቶቹን እርካታ በመጨመር የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ያለመ ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፓርኩ ላይ የሚደርሱና እየደረሱ ያሉ ሰው ሠራሽ አደጋዎችን ለመከላከል እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

ኃላፊው ‹‹ማኅበራቱ አገልግሎቱን የሚሰጡበት የጋራ አሠራር አልነበራቸውም፡፡ ይህም በመሆኑ በየማኅበራቱ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ሲኖሩ ከሀገራዊ ገጽታ ይልቅ ለግል ጥቅማቸው ብቻ ትኩረት አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር›› ብለዋል፡፡

የጋራ አሠራር ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ካሉት የአስጎብኝ ማኅበራት መካከል በአንዱ አባል የሆኑት አቶ ሰሎሞን ኪዴ ‹‹ጥምረቱ በአገልግአሎት አሰጣጡ ዙሪያ ጎብኝዎች ያነሱት የነበረውን ቅሬታ መቅረፍ የሚያስችል ነው›› ብለዋል፡፡ በየማኅበራቱ ይታዩ የነበሩ ውስንነቶችን በጋራ በውይይት ለመፍታት የሚያስችል አሠራር እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹ኃላፊነት የጎደለውን የፓርኩን አያያዝ ችግር ለመቅረፍ ያስችላል›› ያሉት አቶ ሰሎሞን እያንዳንዱ ማኅበር ለፓርኩ ጽዳትና ውበት ያደርግ የነበረው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በፓርኩ ዘጠኝ ማረፊያዎች ያሉ ሲሆን ጥምረቱ በነዚህ ቦታዎች የተሟላ የውኃና የቁሳቁስ አቅርቦት እንዲኖር እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን 32 ሺህ 400 የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ጎብኝተውታል፤ እስከ ኅዳር 2012 ዓ.ም ባሉት ወራት ደግሞ 15 ሺህ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ፓርኩን መጎብኘታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተለይ በማኅበራት የተደራጁ ከዘጠን ሺህ በላይ የአካባቢው ግለሰቦች ደግሞ ከዘርፉ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
ምስል፡- ድረ ገጽ

Previous articleበመስጅድና ቁርአን ላይ የሚደርሱ ቃጠሎዎችን በማውገዝ በመርሳ ከተማ ሠላማዊ ሠልፍ ተካሄደ።
Next articleበክልሉ በድርቅና በተፈጥሮ አደጋ የሚጎዱ አካባቢዎችን መታደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡