
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 17/2012ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ከዚህ በፊት የነበረው የኃይል ተሸካሚ ስብስቴሽኖች ማርጀት እና ዝቅተኛ አቅም መኖር ምክንያት በበርካታ ከተሞች የአምራች ዘርፉን ሥራ መጀመር አላስቻለውም ነበር፡፡
የኃይል እጥረቱ ለኢንቨስትመንት መስፋፋትም ዓይነተኛ ማነቆ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድልም ምንጭ መሆን አልቻለም ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ በመኖሪያ ቤቶች በቂ ኃይል ባለመኖሩ በየወቅቱ ዜጎች ቅሬታ እያሰሙ ለዓመታት የቆዩባቸው ከተሞችም ብዙዎች ናቸው፡፡
በአማራ ክልል ከተሞች የኃይል አቅርቦት እጥረት በየወቅቱ የመልካም አስተዳድር ችግር እየሆነ፣ ዜጎችን ለችግር ያጋለጠ ከአካባቢው መሪዎችም ከአቅም በላይ የሆነ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዜጎች የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ምጥጥን ላይ ቅሬታ እንዲያቀርቡም ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡
የክልሉ የዘውትር ጥያቄ የሆነውና የዕድገት ሰንሰለት መሠረት የሆነው የኃይል አቅርቦት እና የኃይል ምጥጥን ለምን መፍትሔ እንዳላገኘና እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ካሉ በሚል አብመድ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር፡፡
የኮርፖሬሽኑ ትራንስሜሽን ስብስቴሽን ሥራ አስኪያጅ ዘውዱ አስማረ ‹‹የኃይል ምጥጥን ኮታ አይደለም፤ በሁሉም ክልሎች እንደአስፈላጊነቱ በተተከሉ የኃይል ማከፋፈያዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹በአማራ ክልል የሚነሳው ቅሬታ እውነት ነው›› ያሉት አቶ ዘውዱ እጥረቶችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በባሕርዳር ቁጥር 3 አዲስ ሰብስቴሽን ሥራ ጀምሯል፤ 100 ሜጋ ዋትም መጠባበቂያ አለ›› ብለዋል፡፡ ለፋብሪካዎችም ሆነ ለነዋሪው የሚበቃ ስለሆነ በተፈጥሯዊም ሆነ በተቋሙ ችግር መቆራረጥ እንዳይኖር በየወቅቱ የመፈተሽ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ደብረ ታቦር ከተማ ከዚህ በፊት ከ5 እስከ 7 ሜጋ ዋት ብቻ ኃይል ይጠቀም ነበር፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ‹‹ቅሬታውን ለመፍታት የሚያስችል 50 ሜጋ ዋት ኃይል ለመሥጠት በዝግጅት ላይ ነን›› ብለዋል፡፡
‹‹ጎንደር ከተማ የሚነሳው የኃይል አቅርቦት እጥረት ተገቢ አይደለም›› ያሉት ዳይሬክተሩ ጎንደር አዘዞ ሰብስቴሽን ላይ 10 የኃይል ማከፋፈያ ምንጮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በከተማው ግን እስካሁን የተጠቀሙት ሁለቱን ብቻ እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡ ቀጣይ ስምንት ማከፋፈያዎችን ቢጠቀሙ ቅሬታውን ከመፍታት በተጨማሪ መጠባበቂያ ኃይል እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
‹‹የወልዲያ ከተማ 50 ሜጋ ዋት የኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን በቅርቡ ተሠርቷል›› ያሉት አቶ ዘውዱ ከኃይል አቅም ይልቅ የኃይል አገልግሎት አሰጣጡ ላይ በትኩረት መሠራት እንደሚስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ደሴ ከተማ ከዚህ በፊት 32 ሜጋ ዋት ኃይል ተጠቃሚ እንደነበር አስታውሰው አሁን የኃይል እጥረት ችግሩን ለመፍታት ከተማ አስተዳድሩ ገራዶ ላይ 9 ሄክታር መሬት በመፍቀዱ ተጨማሪ 50 ሜጋ ዋት የኃይል አቅም ያለው ማከፋፈያ ስድስት ወርውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ የኃይል አቅርቦት ችግር የለም፤ 230 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሰብስቴሽን ገንብተናል፤ ወደ ኢንዱስትሪዎች የሚሄዱ መሥመሮችን መዘርጋት የክልሉ መንግሥት ድርሻ በመሆኑ የባለሀብቶች ጥያቄ ሊፈታላቸው ይገባል›› ነው ያሉት፡፡ በክልሉ የኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችው ቱለፋ (ሀገረማርያም ከሰም ወረዳ) ላይ ከሁለት ወራት በኋላ አዲስ ሰብስቴሽን ሥራ እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡ ሸዋሮቢት ላይ የሚሠራው አዲስ ሰብስቴሽንም ከጥቂት ቀናት በኋላ ሥራ እንደሚጀምር ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ከተማ ላይ የተቃጠለ ስብስቴሽን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ቁጥር ሁለት 31 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት አቅም ያለው ስብስቴሽን ከሳምንት በኋላ ሥራ ይጀምራል፡፡ ደጀን ላይ አዲስ ሰብስቴሽን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የቡሬ ከተማ ሰብስቴሽን ግንባታም በዕቅድ ውስጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሜሽን እና ሰብስቴሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ አስማረ ‹‹በአማራ ክልል ያለውን የኢንዱስትሪዎችንና የሕዝቡን የኃይል ፍላጎት በቅርብ ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ምላሽ ለመሥጠት በሁሉም አቅጣጫዎቸ እየተሠራ ነው›› ብለዋል፡፡
አዳዲስ የስብስቴሽን ማስፋፍያ እና ነባሮችን የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ በሀገሪቱ ላሉ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት አቅም እንዳለም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ