
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጊዜው 1984 ዓ.ም ነበር። ሕወሃት ሥልጣን እንደያዘ ዓመት እንኳን ሳይሞላው ወሰን መጋፋት፣ ማንነትንም ማጥፋት ጀመረ።
የሕወሃት ሰዎች የአማራውን ወሰን አልፈው፣ ማንነቱንም አጥፍተው ለኔ የሚሉትን ክልል ለማስፋት ይሯሯጡ ነበር። ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ ከጥንተ አማራዊ ማንነታቸው ተነጥለው በኀይል ወደ ትግራይ እንዲካለሉም ተደረገ።
“ዳገት ያበረታው የአማራው ፍኖት” በሚለው መጽሐፋቸው በግፍ ማንነታቸውን የተነጠቁ አማራዎችን በደል እና ጽናታቸውን የሚዳስሱት ዶክተር ቹቹ አለባቸው በ1984 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ላይ በተካሄደው የክልል ክለላ ውይይት ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ ይናገራሉ።
በወቅቱ እና በመድረኩ ላይ የዓይን ምስክር ኾነው ያዩትን እና የታዘቡትን አጫውተውናል። በጎንደሩ መድረክ ላይ አማራ ክልልን የሚወክሉ የኢህዴን ባለስልጣናት ሲኾኑ በሕወሃት በኩል ደግሞ ከፍተኛ አመራሮች እና የጦር መኮንኖች ተሳታፊ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
በመድረኩ ላይ የክልል ክለላ መስፈርቶች ቀረቡ። በመስፈርቶቹ ቅራኔ አልነበረም። ከመስፈርቶቹ ቀጥሎ ከአማራ ተቆርጠው ወደ ትግራይ የሚካለሉ ቦታዎች ዝርዝር ይፋ መደረግ ጀመረ። ይሄኔ የሕወሃትን ሴራ የተረዱ የኢህዴን ሰዎች ተቃውሟቸውን አሰሙ። ተቃውሞው ሲበረታ ስብሰባው “የሻይ ረፍት” በሚል ሰበብ እንዲበተን ተደረገ። በረፍት ሰዓቱ ተቃውሟቸውን ያሰሙ አማራዎች በሙሉ ተመርጠው ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ደረሰባቸው ይላሉ ዶክተር ቹቹ። “ሕወሃት በጦርነት ብዙ ዋጋ ስለከፈለ እነዚህ ቦታዎች ያስፈልጉታል” የሚል ምክንያት እንደቀረበም ዶክተር ቹቹ ያስታውሳሉ።
“ወደ ስብሰባ የገባነው ለማካለል እንጅ የደም ካሳ ለመክፈል አይደለም” በማለት የነቁ የኢህዴን ሰዎች ይኹንታቸውን ነፈጉ። የኾነው ኾኖ በኀይል ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና ጠለምት ከጥንተ አማራዊ ማንነት እና ወሰናቸው ተነጥቀው ወደ ትግራይ እንዲካለሉ መደረጋቸውን ዶክተር ቹቹ ተናግረዋል። ሕዝቡም የማንነቱን መነጠቅ በመቃወም ከፍተኛ መስዋእትነት እንደከፈለ አስገንዝበዋል። ማንነታቸውን በኀይል በተነጠቁት በእነዚህ አካባቢዎች የደረሰው ግፍ የትም ዓለም እንዳልተፈጸም ያስረዳሉ ዶክተር ቹቹ።
“ጥንተ አማራዊ ማንነታችን ይመለስልን” በማለት በፍጹም ሰላማዊነት እና ስክነት ሲጠይቁ ቢኖሩም ሰሚ ግን አጥቶ ቆየ። ጉዳዩ “በፍርድ ከተወሰደች በቅሎየ፣ ያለፍርድ የተወሰደችው ጭብጦየ” ነውና የወልቃይት፣ ጠለምት፣ ጠገዴ፣ እና የራያ ማንነት የመላው አማራ ቀይ መስመር ኾኖ ቀጠለ። የኾነው ሁሉ ኾኖ እነዚህ አካባቢዎች ማንነት እና ወሰናቸውን መልሰው አገኙ። ለዓመታት የናፈቁትን አማራዊ ማንነት ተመልሰው በማግኘታቸው ረኩ። ሲደርስባቸው የኖረውን በደል ሁሉ በይቅር ተው።
እነዚህ አካባቢዎች ወደ ማንነታቸው ከተመለሱ ወዲህ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚያስፈልጋቸው ዓመታዊ በጀት እንኳን አልደረሳቸውም።
ዶክተር ቹቹ ጥንተ አማራነታቸውን መልሰው የተጎናጸፉ አካባቢዎችን ነገር “ለካ ከመጠን ያለፈ ደስታ ምንም ያህል ችግርን ያስረሳል” ሲሉ ገልጸውታል። አሁን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና የጠለምትን ሕዝብ ትልቁ ጉዳያቸው ማንነት እና ወሰናቸው በሕግ ፊት ጸንቶ በሰላም መኖር ነው።
የእነዚህ ሕዝቦች ጽናት ለተምሳሌትነት የሚበቃ ነው ያሉት ዶክተር ቹቹ የፌደራል መንግሥት ይህንን ተገንዝቦ ይዋል ይደር የማይባል ሁለት የቤት ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል። የመጀመሪያው የእነዚህ አካባቢዎች ሀገራዊ ድርሻ የኾነውን በጀት መመደብ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ አካባቢዎች ተመልሰው ያገኙትን ወሰን እና ማንነት በሕግ በማጽናት የሕዝቦችን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ነው።
በወልቃይት፣ጠገዴ፣ ራያ እና ጠለምት ጉዳይ በመንግሥት በኩል ዳተኝነት ሥለመኖሩም ዶክተር ቹቹ መታዘባቸውን ተናግረዋል። የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና የጠለምት የወሰንና የማንነት ጉዳይ የወተትን ንጣት ያህል የጠራ እውነት፣ በተለያዩ ሰዎች የተዛባ ትርክት እና በጊዜ ብዛትም የማይለወጥ ሀቅ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
“ስለወተት ነጭነት ረጅም ንግግር፣ ብዙ ምስክር አያስፈልግም” ያሉት ዶክተር ቹቹ ስለወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና ጠለምት የወሰንና የማንነት ጉዳይ መነጋገር ጉንጭን ማልፋት ቢኾን እንጅ እውነታው ግን በመንግሥትም፣ በሕወሃት እና በትግራይ ህዝብም፣ እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የማይደበቅ ነው ብለዋል።
ይህንን በውል በመገንዘብ የፌደራል መንግሥት የእነዚህን አካባቢዎች ታወቆ ያደረ ወሰን እና ማንነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕግ በማረጋገጥና በማጽናት ሕዝቡ በሙሉ ልብ ወደ ልማት እንዲገባ ማስቻል እንዳለበትም ዶክተር ቹቹ አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!