ኢትዮጵያ በሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከዩጋንዳ ጋር ታደርጋለች

95

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ይጫወታል።
ውድድሩ ዛሬ በታንዛንያ ዳሬሰላም ይጀመራል።

ታንዛንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ዛንዚባር፣ ዩጋንዳ እና ብሩንዲ ይሳተፋሉ።

በውድድሩ የመክፈቻ ቀን በቻማዚ ስታዲየም ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ትጫወታለች።

የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ታንዛንያ ልምምዳቸውን ትናንት በኡሁሩ ስታዲየም አድርገዋል።

ቡድኑ ለውድድሩ በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ እና ረዳቶቻቸው እየተመራ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያከናውን ቆይቷል።

በዝግጅቱ ወቅት የተለያዩ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ከአገር ውስጥ ክለቦች ጋር አድርጓል።

በአሰልጣኝ አዩብ ከሊፋ ኪዪንጊ የሚሰለጥነው የዩጋንዳ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።

በዩጋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አግነስ ሙጌና የተመራው ልዑካን ቡድን ከትናንት በስቲያ ታንዛንያ ገብቷል።

በዩጋንዳ ቆይታውም ከአገር ውስጥ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አድርጓል።

የውድድሩ አዘጋጅ ታንዛንያ ከብሩንዲ ከቀኑ 9 ሰአት በቻማዚ ስታዲየም የመክፈቻ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ሰባት አገራት ውድድራቸውን በሁለት ምድብ ተከፍለው እንዲያደርጉ መርሐ-ግብር ወጥቶላቸው ነበር።

ይሁንና ኬንያ እና ሩዋንዳ አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኑ በመሆናቸው ምክንያት ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን አሳውቀዋል።

በዚህም ምክንያት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት የውድድሩን ፎርማት በመቀየር አምስቱ አገራት እርስ በእርሳቸው የሚጫወቱበትን አማራጭ (round robin format) ለመጠቀም ተገዷል።

በእርስ በእርስ ጨዋታው የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው አገር የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን ሌሎቹ አገራት እንደ ውጤታቸው ደረጃቸውን ያገኛሉ።

ውድድሩ በቅድሚያ በኬንያ ሊደረግ የነበረ ቢሆንም ለውድድሩ ማስኬጃ የተመደበው ገንዘብ በመዘግየቱ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ ነበር።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የሴካፋ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በኮትዲቭዋር አቢጃን ባደረገው ስብስባ ውድድሩ በታንዛንያ እንዲካሄድ ወስኗል።

የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ነሐሴ 1/2015 ይቆያል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀመረ።
Next article“ስለወተት ነጭነት ንግግርም፣ ምስክርም አያስፈልግም” ዶክተር ቹቹ አለባቸው