
አዲስ አበባ: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየሠራ የሚገኘዉን የሪፎርም ሥራ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎቹ የምርምር ዩኒቨርሲቲ፣ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ፣ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ በማለት በተልእኮ እና በትኩረት መስካቸዉ እንዲከፈሉ ተደርጓል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ያሉ ዩኒቨርስቲዎች 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች፣ 15 አፕላይድ፣ 22 አጠቃላይ ዩኒቨርስቲዎች፣ 2 የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ እና 1 የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መኾናቸዉንም ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በቀጣይ በሁሉም መስኮች ትምህርት ከመስጠት ይልቅ የተሻለ ትምህርት በሚሰጡባቸዉ የትምህርት አይነቶች እንዲገደቡ ይደረጋል ነዉ ያሉት።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ሁሉንም ማስተማራቸዉ አማካኝ ዉጤት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረጉን አንስተዉ ይህ ደግሞ የትምህረት ጥራቱ ላይ ጫና አሳድሯል ብለዋል። ይህ ልየታ ግን ተቋማቱ ባላቸዉ የኢኮኖሚ እና የማስተማር አቅም ተለይተዉ በየዘርፋቸዉ ትምህርት እንዲሰጡ ማድረግን አላማ ያደረገ ነዉ ሲሉ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው እንዳሉት የልየታ ሥራው በ2014 ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን በ2016 በሰፊዉ ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።
የትምህርት ተቋማቱ በአካባቢዉ ያለዉን ሀብት ታሳቢ በማድረግ ይሠራሉ ብለዋል። በተጨማሪ ከዚህ በፊት ለትምህርት ጥራት እንዲያግዝ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ መሠራቱን እና የትምህርት ርዝማኔዉን ወደ 4 ዓመት ማሳደግ ላይ መሠራቱንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ ከግብአት ማሟላት በተጫማሪ የዩኒቨርሲቲ መሪዎች ለቦታዉ በሚመጥን መልኩ በማወዳደር እየተሠራ መኾኑን የትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ሳሚኤል ክፍሌ ተናግራዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ግኡሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!