
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ከሩሲያ የፌደራል ማዕድን ኤጀንሲ ሚኒስትር ኢቭጌኒ ፔትሮች (ዶ.ር) ጋር ተወያይተዋል።
ሁለተኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ በተያዘው ሳምንት ማገባደጃ ላይ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ልዑክ አባል ሆነው በጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።
የኢትዮ – ሩሲያ በይነ መንግስታት የጋራ ኮሚሽን ጥምር ሰብሳቢ የሆኑት ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ ከሩሲያ የፌዴራል ማዕድን ኤጀንሲ ሚኒስትር ኢቭጌኒ ፔትሮቭ ጋር በሞስኮ ከጉባኤው ጎን ለጎን ስለሚፈረሙ የሁለቱ አገራት ስምምነቶች፣ በቀጣይ ስለሚጠበቁ ስምምነቶች ያሉበትን ደረጃ አስመልክቶ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
የሁለቱ አገራትን የኢኮኖሚ ግንኙነት የማጠናከር፣ የንግድ ምክር ቤቶችን የሚያሳትፍ ፎረም የሚዘጋጅበትን ሁኔታ መፍጠር፣ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን፣ በስፔስ ሳይንስ ጥናት፣ በአቅም ግንባታ፣ በምርምር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ እና በጋራ ስለሚሰሩ ዘርፈ ብዙ አጀንዳዎች መክረዋል።
በጉባኤው ኢትዮጵያ እና ሩሲያን የተመለከቱ የጎንዮሽ ውይይቶች እንደሚደረጉና የጋራ ስምምነቶች በሀገራቱ መካከል እንደሚፈረሙም ይጠበቃል።
በሩሲያ ተመራማሪዎች ላለፉት 35 ዓመታት በኢትዮጵያ ይካሄድ ለነበረው የባዮሎጂካል ቅኝትና ጥናት ስራን በጋራ ለማካሄድ የጋራ ጥናት ማዕከል ማቋቋሚያ ሰነድ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ተቋማትን የተመለከቱ ጉዳዮች ይፈረማሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል እንደሆኑም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!