136 ተቋማት ከመደበኛ በጀታቸው ከ10 በመቶ በላይ አልተጠቀሙም።

52

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ136 ተቋማት ላይ ባደረገው የ2014 በጀት ዓመት የኦዲት ሥራ ተቋማት መንግሥት ከበጀተላቸው መደበኛ በጀት ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ ጥቅም ላይ አለማዋላቸውን አስታወቀ፡፡ ከመደበኛ በጀት 35 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ እንዳላዋሉም ገልጿል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ብርሃኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባደረገው ኦዲት በ136 የፌዴራል ተቋማት መንግሥት ለ2014 በጀት ዓመት ከበጀተላቸው መደበኛ በጀት ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ መጠቀም እንዳልቻሉ ተረጋግጧል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ165 ተቋማት ላይ የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በተመለከተ የኦዲት ሥራ መሥራቱን የገለጹት አቶ ወንድወሰን፤ የኦዲት ሥራ ከተሠራባቸው 165 የፌዴራል ተቋማት ውስጥ 73 ተቋማት ጥሩ አፈጻጸም በማሳየታቸው ነቀፌታ የሌለውና ጥሩ አስተያየት የተሰጣቸው ሲሆን፤ በ66 ተቋማት ላይ ጥቂት የኦዲት ግኝት ስለተገኘባቸው አጥጋቢ አስተያየት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ስድስት ተቋማት ላይ አስተያየት ለመስጠት የማይቻል የኦዲት ግኝት የተገኘ ሲሆን 19 ተቋማት ላይ በተደረገ የኦዲት ሥራ የጎላ ችግር ያለባቸው ሆነው በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት እንደተሰጣቸው አብራርተዋል።
በ2014 ዓመት በጀትን ሥራ ላይ ያለማዋል የኦዲት ግኝት ከተገኘባቸው ተቋማት ውስጥ፦

👉የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ስምንት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን፣

👉የገንዘብ ሚኒስቴር ስድስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን፣

👉ጤና ሚኒስቴር ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን፣

👉የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን እና

👉የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አንድ ቢሊዮን ብር እንዲሁም ሌሎች ተቋማትም እንደሚገኙበት አመላክተዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡

ተቋማቱ ከተበጀተላቸው የ2014 በጀት ዓመት ውስጥ አምስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ከመደበኛና 28 ቢሊዮን በድምሩ 35 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ እንዳላዋሉ አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ በሚያደርገው የኦዲት ሥራ በተቋማት ላይ ተለዋዋጭ የኦዲት ግኝት ማለትም አንድ ዓመት ከፍና በሌላ ዓመት ዝቅ የማለት ችግር እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የተገኘባቸውን ገንዘብ ለመንግሥት መመልስ የሚችሉ ተቋማት እንዲመልሱ፣ መመለስ የማይችሉት በሕግ እንዲጠየቁ የሚል አቅጣጫ ምክር ቤቱ መስጠቱን ጠቁመው፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሰጠውን አቅጣጫ ተፈፃሚ የማድረግ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ የተሰጠው የማስተካከያና ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ አስተያየት ውጤት ከቀጣይ በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ጋር አብሮ የሚቀርብ ይሆናል ሲሉም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ትሳተፋለች።
Next articleየኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ከሩሲያ የፌዴራል ማዕድን ኤጀንሲ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።