
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ትሳተፋለች፡፡
የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከሐምሌ 26 እስከ 28 ቀን 2023 የሚካሄድ ሲሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ መሪዎች ልዑክ አባል ሆነው በጉባኤው ይሳተፋሉ።
በጉባኤው ከአፍሪካ ሩሲያ ጉዳዮች ባሻገር የኢትዮ ሩሲያን የተመለከቱ የጎንዮሽ ውይይቶች የሚደረጉና የጋራ ስምምነቶች በሀገራቱ መካከል እንደሚፈረሙ ይጠበቃል።
ኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል የተዘጋጀውን ፍኖተካርታ እና በሩሲያ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ላለፉት 35 ዓመታት በኢትዮጵያ ይካሄድ ለነበረው የባዮሎጅካል ኤክስፔዲሽንና ጥናት ሥራን በጋራ ለማካሄድ የጋራ ጥናት ማዕከል ማቋቋሚያ ሰነድን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ተቋማትን የተመለከቱ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮ-ሩሲያ በይነ መንግሥታት የጋራ ኮሚሽን ጥምር ሰብሳቢ የሆኑት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) እና በሩሲያ የፌዴራል ማዕድን ኤጀንሲ ሚኒስትር የቭጌኔ ፔትሮቭ (ዶ.ር) በሩሲያ ሞስኮ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ከመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ስለሚፈረሙ የሁለቱ ሀገራት ስምምነቶች፣ ያላለቁና ለወደፊት አልቀው ይፈረማሉ ተብሎ ስለሚጠበቁ ስምምነቶች የደረሱበትን ደረጃ የተመለከተ መረጃ መለዋወጣቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!