
ሁመራ: ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። የወልቃይት ወረዳ በውስጥ ገቢ፣ ከወረዳው ሕዝብ እና ከአካባቢው ተወላጆች በተሰበሰበ ገቢ ያስገነባቸውን የመሠረተ ልማት ሥራዎች አስመርቋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ትግል የፍትሕ፣ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች ነበሩት የሚሉት የወልቃይት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ክብረአብ ስማቸው “አማራ ነን የምንለው ከአማራነት ውጭ ሌላ ማንነት ስለሌለን ነው” ብለዋል። ከከፋኝ የትጥቅ ትግል እሰከ ሕጋዊ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለነጻነቱ እና ለማንነቱ ያላደረገው ጥረት እና ተጋድሎ አልነበረም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ወያኔ ከሰላም አማራጮች ይልቅ አፈሙዝን መምረጡ ውድቀቱ እንዲፋጠን አድርጎታል ብለዋል።
ወያኔ የሕዝብን ጥያቄ በሰለጠነ መንገድ ከመመለስ ይልቅ በወልቃይት ሕዝብ ላይ ከቅኝ ግዛት ዘመን በከፋ መልኩ ሞት፣ እስር፣ ማፈናቀል፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ አፈና እና ምጣኔ ሃብታዊ አሻጥር ፈጽሞበታል ብለዋል።
ከትግራይ የተነሱ ጠባብ የብሔር ፖለቲከኞች በሰለጠነው 21ኛው ክፍለ ዘመን በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የፈጸሙት የዘር ማጽዳት ወንጀል እና የምጣኔ ሃብታዊ አሻጥር አሳፍሪም፣ አስፈሪም፣ ነውርም ነበር ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ነጻነቱን በትግሉ ካረጋገጠ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል ነው ያሉት።
ከነጻነት ማግስት የምንገኝበት ነባራዊ ኹኔታ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት፤ የሕዝብን ሥነ-ልቦና ከጦርነት አዙሪት እና ነጋሪት ጉሰማ ማውጣት የሚጠይቅ ነበር ያሉት አቶ ክብረአብ በፈተና እና ፈታኝ ጊዜ ውስጥም ኾነን ማልማት እና መሥራት እንደምንችል አሳይተናል ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በስደት፣ በሞት፣ በወከባ እና በአፈና ውስጥ ኾኖ የሚጠይቃቸው የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች በሕዝብ ትግል ተመልሰዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በአንድ እጃችን እያለማን በሌላ እጃችን ለነጻነታችን የሚያስፈልገውን መሰረታዊ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።
የሕዝብን ተፈጥሯዊ የማንነት እውቅና እና የበጀት መብት ጥያቄዎች መመለስ የመንግሥት መሠረታዊ ኅላፊነት ነው ያሉት አቶ ክብረአብ በተረፈ ግን ከሰማይ በታች የወልቃይቴን አማራነት መደፍጠጥ የሚችል ምንም ኃይል እንደማይኖር እርግጠኞች ነን ነው ያሉት።
ወልቃይት ጠገዴ የከረሙ እና ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ አውቋቸው ያደሩ ጥያቄዎቻችን እስኪመለሱ ድረስም በራስ አቅም ማልማት እና ሕዝብን ማገልገል እንቀጥላለን ብለዋል።
ዛሬ ከምናስመርቃቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች በተጨማሪ ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለመገንባት ዕቅድ አለ ያሉት አሥተዳዳሪው መንግሥት፣ ሕዝቡ እና በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የሚችሉትን ሁሉ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!