ፋሲል ከነማ ውበቱ አባተን አሠልጣኝ አድርጎ ሾመ።

29

አዲስ አበባ: ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ)አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ፋሲል ከነማን ድጋሜ ለማሠልጠን መስማማታቸው ቀድም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።

አሠልጣኙ ዛሬ በይፋ ለ3 ዓመታት አፄዎቹን ለማሠልጠን ፊርማቸውን አኑረዋል።

ዛሬ በነበረው የውል ስምምነት የክለቡ ፕሬዚዳንት ባዩህ አቡሃይና የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብርሃኑ የተገኙ ሲሆን ከንቲባ ባዩ አቡሃይ ፋሲል ከነማ የተሻለ ቁመና እንዲኖረው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት እየሠራ ነው ብለዋል።

ክለቡ በተለይ ከባለፈው አመት ከነበረበት የውጤት መንሸራተት ወጥቶ በቀጣይ ወደ ቀድሞ ከፍታው እንዲመለስና የያዝናቸውን የረዥም ጊዜ እቅዶች ለማሳከት በማሰብ አሠልጣኝ ውበቱ አባተን መቅጠራቸውን ተናግረዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በኮንትራታቸው ሁለተኛ ዓመት (በ2017 ) ዋንጫ የማንሳት ግዴታ እንዳለባቸውም አቶ ባዩ ተናግረዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ፋሲል ከነማን ድጋሜ የማሠልጠን እድል በማግኘታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግተዋል። ፋሲል ከነማን የሚመጥን ቡድን ለመገንባት ቁርጠኛ መኾናቸውን ነዉ አሠልጣኙ የገለጹት። ቡድኑን በራሳቸው ፍላጎት የመገንባት ነፃነት እንደተሰጣቸውና በተለይ ወጣት ተጫዋቾችን ማፍራት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ከደጋፊዎች ጋር በተያያዘ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብርሃኑ በቦርዱና በደጋፊዎቹ መካከል የተለየ ልዩነት እንደሌለ ገልጸው ከውጤት መጣት ጋር በተያያዘ ያሉ ልዩነቶችን በውይይት እየፈታን እንቀጥላለን ብለዋል።

ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲሠሩ አሳሰቡ።
Next articleበሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ።