
ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም ስምንት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ ፕሮፌሰሮች የእውቅና ዝግጅት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ፕሮፌሰሮች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና የፕሮፌሰሮቹ ቤተሰቦች በተገኙበት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እያደገ ስለመጣው የፕሮፌሰሮች ቁጥር ደስተኛ መሆናቸውንና በፕሮፌሰሮች እንደ ተቋም እንደሚኮሩ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ፕሮፌሰርነት ለሙያው መኖርን ይመለከታል ሲሉ በመግለጽ የበለጠ ኃላፊነት እና ትጋትን መቀበል መኾኑን ጠቁመዋል።
ዶክተር ፍሬው ተገኘ በመክፈቻ ንግገራቸው እውቅና የተሰጡ ፕሮፌሰሮችን እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ60 ዓመት ጉዞው 30 ፕሮፌሰሮችን ማፍራቱን በመጠቆም በብዛትም ሆነ በጥራት ማደግ ይኖርበታል ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ በማከልም እናንተ ፕሮፌሰሮች ለዚሁ ደረጃ የደረሳችሁት እንዲሁ አይደለም እና ያላችሁን ግላዊ ግንኙነት ወደ ተቋማዊ አጋርነት ማሳደግ ይጠበቅባችኋል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዕውቅና ያገኙ ፕሮፌሰሮችም:- ፕሮፌሰር ነጻነት ፈንታሁን፣ ፕሮፌሰር አመራ ሰይፉ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ዓለማየሁ፣ ፕሮፌሰር ንጉሱ ገበየሁ፣ ፕሮፌሰር አረጋ ባዝዘው፣ ፕሮፌሰር ፀጋዬ ካሳ፣ ፕሮፌሰር መላኩ ዋለ እና ፕሮፌሰር ሰይፉ አድማሱ ናቸው፡፡
በዝግጅቱም ፕሮፌሰሮች ሀሳባቸውን፣ ልምድና ተሞክሯቸውን በማቅረብ በዝግጅቱ ላይ በታደሙ እንግዶች እና ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ዶክተር ፍሬው ለፕሮፌሰሮች ስጦታ ያበረከተላቸው መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!