በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚታዩ ሐሰተኛ መረጃዎች ለመደበኛው የመገናኛ ብዙኃን እና ለጋዜጠኞች ፈታኝ እየኾኑ መምጣቸው ተገለጸ።

20

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሹሻ – አዘርባጃን በተካሄደው “የሹሻ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ፎረም” የማኅበራዊ ሚዲያ እና መደበኛው ሚዲያ ያላቸው መስተጋብር እና ሐቅን በማፈላለግ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት ምክክር ተካሂዷል።

ሐሰተኛ እና የተሳሳተ መረጃን ለማስወገድ መደበኛው ሚዲያ በሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቁሟል።

ጊዜው የማኅበራዊ ሚዲያውን በስፋት መጠቀም የሚፈልግ በመኾኑ መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው በሹሻ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ፎረም ላይ ተናጋሪ ሆነው የቀረቡት የ“ዲጂቲፕስ” የተሰኘው የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማቲያስ ሉፍኪንስ ገልጸዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያውን እንደስጋት ከመቁጠር እንደዋነኛ መንገድ ማሰብ መጀመር ያስፈልጋልም ብለዋል።

በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚታዩ ሐሰተኛ መረጃዎች ኃላፊነት የጎደላቸው እየሆኑ መምጣታቸው ለመደበኛው የመገናኛ ብዙኃን እና ለጋዜጠኞች ፈታኝ እየሆኑ መምጣቸውን በማንሣት የሞገተው ደግሞ የቲአርቲ ወርልድ የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ኦውባይ ሻህባንዳር ነው።

ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን በመረጃ ማጥራት፣ የሐሰተኛ መረጃ ምንጮችን መለየት እና መረጃዎችን በኃላፊነት ማጋራት ላይ መሥራት እንደሚገባቸው በጋዜጠኝነት ለ30 ዓመታት የሠሩት እና በአዘርባጃን የኤዲኤ (ADA) ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት መምህርነት እየሠሩ የሚገኙት ሻፋግ ማሂራሊዬቫ ገልጸዋል።
በተለይ የጥልቅ ሐሰተኛ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ለጋዜጠኝነት ትልቅ ፈተና መሆኑም ተነሥቷል።

ኢቢሲ እንደዘገበው በሹሻ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ፎረም ላይ ከ49 ሀገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ ጋዜጠኞች፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች እና የዘርፉ ተመራማሪዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወልድያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ዙር የ12ተኛ ክፍል የ2015 ዓ.ም ተፈታኝ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው።
Next articleአልማ በእብናት ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ያስገነባው ባለ ሦስት ፎቅ የመማሪያ ህንፃ ተመረቀ።