የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ላይ ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ ከ88 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

50

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በ1971 ዓም በዩኔስኮ ተመዝግቧል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅየ የዱር አንስሳት ባለቤትም ነው፡፡
ፓርኩ ፦

👉 412 ስኩዮር ኪሎ ሜትር ሥፋት አለው፡፡

👉 በውስጡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን ዋልያን ጨምሮ ጭላዳ ዝንጅሮ፣ የሚኒሊክ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮና ሰሳ አቅፎ ይዟል፡፡

👉 ከ20 በላይ አጥቢ አንስሳት በውስጡ አሉ፡፡

👉 ከ1 ሺህ 200 በላይ የእጽዋት ዝርያዎችን ይዟል፡፡

👉 ከ180 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች አሉት፤ ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙ ከፓርኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

👉 በሰሜን ጎንደር ዞን ሥር የሚገኙ አምስት ወረዳዎችንም ያስተሳስራል፡፡

👉 ፓርኩ በተደጋጋሚ ባጋጠመው የእሳት አደጋ ችግር ለጉዳት በመጋለጡ መልሶ የሚያገግምበት ተግባር እየተሠራም ይገኛል።

👉የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኀላፊ አዛናው ከፍያለው በፓርኩ ውስጥ ባለፈው ዓመት ከተተከሉ 25 ሺህ ችግኞች ውስጥ 88 በመቶ ችግኞች መጽደቃቸውን አንስተዋል፡፡

አቶ አዛናው የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የልቅ ግጦሽ መስፋፋት፣ የእርሻ ቦታ እጦት፣ የመንገድ ጥገና፣ በሕገወጥ መንገድ የኢንቨስትመንት መሥፋፋት ቦታው ለችግር እንዲጋለጥ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡

ቦታውን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የበርካታ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነውም ብለዋል፡፡

አምስቱ ወረዳዎች የዞኑ እንዲሑም ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ ቢሠሩ ችግሩ እንደሚቀረፍም አስገንዝበዋል፡፡

አቶ አዛናው እንዳሉት ችግኞቹ ከመፈላታቸው በፊት የትኞቹ ችግኞች ለቦታው አስፈላጊ እንደኾኑ ጥናት ተደርጎ፣ ጉድጓዱ ሲቆፈር ኀላፊነት የሚወስዱ ሰዎች ተመርጠው በተከላ ወቅትም የአየር ሁኔታው ተጠብቆ እንደተተከለ አስረድተዋል፡፡
በብዛት ኮሶ ዛፍ እንደተተከለ የሚናገሩት አቶ አዛናው ችግኙ ከአካባቢው ጋር የሚስማማ እና የአየር ንብረቱን የሚቋቋም ነው ብለዋል፡፡

የብዝኃ ሕይዎቱን ለማስቀጠል እና የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ለማድረግ ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ የማድረግ ሥራ በሥፋት እየተሠራ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

ችግኞችን ለሚጠብቁ፣ መትከያ ለሚቆፍሩ እና ለሚተክሉ አካላት ኮር አፍሪካ ዋይድ ፋውንዴሽን ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ በሐምሌ 17/2015 ዓ.ም ዕትሟ
Next articleደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገች።